ጥቁር እንግዳ
| 08.05.20
Copyright © 2019 House of Guramayle
All rights reserved.
ISBN: 978-1-78972-563-6
ስጦታ
ይህ መጽሐፍ ውብ ለሆነው
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ማኅበረሰባችን ተበርክቷል።
ከተጋሩ ቃላት መጽናናትን እና ጥንካሬን ያገኙ፡፡
ፍቅርን በእውነት እንኑር!
ምስጋና
ለዚህ መጽሐፍ እውን መሆን አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ ማመስገን እንወዳለን፡፡
ስለ ታሪኮችዎ እርግጠኛነት ስላመኑልን እናመሰግናለን ፡፡
መግቢያ
When we set out to make this book, an idea that has been in development since 2017; we were not even sure if we would get submissions. People have reached out to House of Guramayle over the years, confiding their personal stories and experiences to us and we realized how powerful and brave an act this was, but of course it is one thing to share such personal accounts in a private setting whether that is virtual or not and it is quite another to have personal experiences shared to a wider audience. House of Guramayle aims to create a safe space for members of the LGBTQ+ community and we acknowledged that it would take a lot of trust to request that people be open to the chance to elevate their stories
and experiences on a global platform from something they have either only shared with themselves or with individuals they have put trust in. Our queer identities
continue to be challenged by wider society and harmful policies in Ethiopia that seek to dehumanize us and erase our lived experiences. The false narrative that identifying as LGBTQ+ is a Western import is one of many misguided ideas around what it means to be Ethiopian and Queer, our only import has been homophobia. We only have to look at the history in our country which has a rich tapestry of diverse ethnic groups to see that Queer experiences have always existed and will continue to exist.
Walatta Petros for example was a 17th century Ethiopian nun who was said to have had an intense and lifelong relationship with another nun, her biography contains the
earliest known depiction of same sex desire among women in East Africa. The Maale, Harari and Asmara people are among some ethnic groups in Ethiopia that have been documented by researchers for exploring sexual and gender roles fluidly.
Christianity was introduced to Ethiopia in the 4th century, over 60% of Ethiopians identify with a Christian faith and over 33% identify as Muslims. Religious leaders hold a lot of power and influence in Ethiopian society, their teachings are followed with deep rooted unquestionable belief which blurs the lines between faith and facts. This blurring of lines makes for the perfect breeding ground of misinformation and fear to thrive.
Most LGBTQ+ Ethiopians will have grown up in communities that center religion in their daily lives. The internalized shame and guilt around sexual and gender
identities without the space to challenge and reshape what faith means results in exploring sexual and gender identities in such conflicting settings. This undeniably causes a lot of pain and having multiple identities co-existing peacefully is an even smaller space to be occupied, by that I mean the ability to identify with a faith whilst also identifying as LGBTQ+.
There is great power in story telling for it enables us to hold a mirror up to ourselves to be seen and see others in as authentic selves, to be relatable and to learn from one another. Books were a constant source of companionship for me through my own journey of coming to terms with my Queer identity,
I would get lost in worlds and characters that made me feel less alone because I could relate to the human experiences on the page.
The lack of intersectionality in literature is problematic, finding stories that represent marginalized human beings as fully dimensional and not portrayed solely as a product of their trauma (however valid that may be) is challenging. Those limiting narratives do not show the ability and/or potential to thrive, not just survive.
It is essential that we are telling stories that explore the full spectrum of our humanity to keep us moving forward.
Growing up we did not have stories to read that represented us and this book is a chance for that. By taking control of our own narratives and sharing them, we are telling the world and ourselves that our stories matter because we matter. We are thankful for those members in our community who submitted their stories for this collection and hope that this book of stories will dispel
myths whilst giving an insight into the different lives of Queer Ethiopians.
Zelly Lisanework
Edit
ያልታወቀ 1
ብዙ ጊዜ ከጓደኞቼ፣ ከማላውቃቸው እንግዳ ሰዎች፣ ከኤክትሮኒክስም ሆነ የኅትመት ሚዲያዎች፤ ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሰምቻለሁ። አንዳንዶቹ በጭፍን ጥላቻ ተነሣስተው፣ ሌሎች የተሳሰተ መረጃ ይዘው አለዚያም በቂ ጥናት ሳያደርጉ የመሰላቸውን ሃሳብ እንደ ትክክለኛ እና እንደ ተረጋገጠ እውነታ ያለ ምንም ተጠያቂነት በሕዝመገናኛ ብዙኀን እስከ ማቅረብ ደርሰዋል። ምንም እንኳን ስለሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማሳሰብ ያለፈ አቅም ባይኖረኝም የራሴን እውነታ በመናገር የተቻለኝን ለማድረግ ወሰንኩ።
ተወልጄ ያደግሁት በሰሜናዊዉ የአገሪቷ ክፍል በምትገኝ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። አስተዳደጌ ከማንኛውም ልጅ የተለየ አልነበረም። አንድ በተደጋጋሚ የሰማሁት ነገር ቢኖር ከእናቶቻቸው ጋር ብቻ ያደጉ ወንድ ልጆች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እንደሚሆኑ ነው፤ እውነት ለመናገር እኔም ያደግሁት እናቴ ጋር ነው። ሆኖም ግን እናቴ እኔን ብቻ ሳይሆን 4 ወንድሞቼንም ጭምር ብቻዋን ነው ያሳደገችን፤ ስለዚህ አምስታችንም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን መሆን ነበረብን። እስከማውቀው ድረስ ግን አራቱም ወንድሞቼ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን አይደሉም። በዚህ ፍልስፍና መሠረት ብዙዎቹ የጎረቤት ልጆችም ሆኑ እናቶቻቸው ጋር ብቻ ያደጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ናቸው ማለት ነው። ሁለተኛው መላ ምት ደግሞ “በልጅነታቸው ተደፍረው ነው።” የሚባለው ነው።
ስለ ሌላው ሰው መናገር ባልችልም፤ እኔ ተደፍሬም ሆነ ያለ አግባብ ተነክቼ አላውቅም። አንድ ሰው ስለ ተደፈረ ፆታዊ ተማርኮውን ይቀይራል ብዬም አላምንም። ሌላኛው መላ ምት ደግሞ “ከፊልም ወይም ከሌላ ሰው ተምረውት ነው።” የሚባለው ነው። ሲጀመር እንኳን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ታሪክ እና የወሲብ ትዕይንት ያለበት ፊልም ቀርቶ ወንድ እና ሴት እንኳን ሲሳሳሙ እንድናይ ስለማይፈለግ የሕንድ ፊልም ወይም የልጆች ጊዜ ካልሆነ “ታላቅ ፊልም” እንኳን እንድናይ አይፈቀድልንም ነበር። ዘመናዊነት መስሏቸው ጀመሩት የሚለው ለእኔም ሆነ በቅርበት ለማውቃቸው ጓደኞቼ አይሠራም።
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን ያወቅሁት ዕድሜዬ ለአቅመ-አዳም በደረሰበት ወቅት ነበረ። አብዛኛዎቹ ጓደኞቼ ለተቃራኒ ፆታ ፍላጎት ማሳየት ሲጀምሩ እኔም ለተመሳሳይ ፆታ ፍላጎት እንዳለኝ ተረዳሁ። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ፤ በየዕለቱ ጧት ማታ ጸሎቴ ሆነ ስእለቴ ፈጣሪ እንዲቀይረኝ ነበር። ከፆም፣ ጸሎት እና ስእለትም ባለፈ ለመቁጠር ለሚያደግቱ ጊዜያት ወደተለያዩ አድባራት እና ገዳማት በመሔድ ፀበል በተደጋጋሚ ተጠምቄያለሁ። በዚህም ለውጥ ባለማየቴ ሃይማኖቴን እስከ መቀየር እና ፕሮቴስታንት እስከ መሆን ደርሼ ነበር። ሆኖም ግን ምንም ያህል ባልጸልይ እና ብጸልይ ምንም የተቀየረ ነገር የለም። የአእምሮ እረፍትና ሰላም ያገኘሁት ራሴን በጸጋ በተቀበልኩበት ወቅት ብቻ ነው።
እንደ መደምደሚያ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር፤ ማን ከቤተሰቡ ለመቆራረጥ፣ በማኀበረሰቡ ለመጠላት እና ለመገለል፣ በቤተ-እምነት ለመወገዝ፣ “በፈጣሪ ለመኮነን” ሆነ በሕግ ለመወንጀል ይመርጣል? እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ መርጠን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን አልሆንም። እኛን ለመቀየር ከሞመከር ለመረዳት መሞከሩ እጅግ በጣም ቀላል ስለ ሆነ፤ ጭፍን ጥላቻን አስወግደን ለመረዳዳት ብንሞክር ይሻላል ባይ ነኝ።
የ BAKI ታሪክ
ሰላም! ባኪ እባላለሁ፡፡ የ31 ዓመት ወጣት ስሆን ልክ እንደ ማንኛውም ሰው ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚያውቋቸው የራሴ የሆኑ ምሥጢሮች አሉኝ፡፡ ለምን ምሥጢር ሆነ? ይመስለኛል… ሰዎች በባህሪያቸው የራሳቸው ባልሆነ ጉዳይ ጣልቃ ስለሚገቡ፡፡ በኢትዮጵያዊ ቤተሰብ የልጆችን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ የራሱን ሃሳብ፣ የሕይወት ፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ምርጫና ሌሎችንም ነገሮች ሁሉ በልጆቹ ላይ መጫን እንደ ባህል ነው የሚታመነው፡፡ እኔም የክርስትና ሃይማኖት በሚከተል ቤተሰብ ውስጥ በማደጌ ከዚህ የተለየ ነገር የለኝም፡፡
ሁለቱም አምነውልን ባያውቁም ወላጆቼ ከእህትና ወንድሞቼ በላይ እኔን አብልጠው ይወዱኛል፡፡ ልጅ እያለሁ ለአስተዳደግ አስቸጋሪ አልነበርኩም፡፡ እናቴ ከሁሉም ቤተሰብ ውስጥ የተባረክሁ እና ጨዋ እንደ ሆንኩ ሁልጊዜ ትናገር ነበር፡፡ አባቴም በጭራሽ ተበሳጭቶብኝ አያውቅም፤ ሁልጊዜም እንደሚኮራብኝ ይነግረኝ ነበር፡፡ ሕፃን እያለሁ ብዙ ነገር አያስጨንቀኝም ነበር፡፡ ደስተኛ ልጅ ነበርኩ፡፡ ከሕይወት የምፈልገው ነገር የማያቋርጥ ደስታን እና የዓለምን ሰላም ብቻ ነበር፡፡
የሕይወቴ አስቸጋሪ መንገድ የጀመረው ሳድግ ነበር፡፡ ሁላችንም ደስተኛ እና የምንኮራበትን ሕይወት መኖር የዕለት ዕለት እንቅስቃሴአችንን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን እንደዛ አልነበርኩም፡፡ አብዛኛውን ሕይወቴን የከፋ ነገር ውስጥ ነበርኩ፡፡
ከፍተኛ ድብርት ከጉርምስና ዕድሜዬ ጀምሮ የወጣትነት ጊዜዬን በሙሉ የሕይወቴ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለድብርቴ ምክንያቱ ደግሞ መደበቄ ነበር፡፡ የተለየሁ መሆኔን እያወቅሁ እንኳን ምሥጢሬን በራሴ የምጋፈጥበት አቅሙ አልነበረኝም፡፡ አንድ ቀን አንድ ሰው ስለ እኔ ቢያውቅ መጨረሻዬ እንደ ሆነ አውቃለሁ፡፡ ማኅበራዊ ሕይወቴ፣ ለራሴ ያለኝ ግምት፣ እምነቴ፣ መኖሬ እንዲሁም ከመላው ቤተሰቤ ጋር ያለኝ ግንኙነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ እረዳለሁ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በሁለቱም ወላጆቼ፣ ከእህት እና ወንድሞቼ ጋር በጤናማ እና ግብረ-ገባዊ ክርስትና ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ አንድ ዓይነት መንገድ ብቻ እንድከተል ምርጫ ሰጥቶኛል፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ፡፡ ወላጆቼ ለእኔ ካወረሱኝ ዕሤቶች ውስጥ ሁልጊዜም ቢሆን ፈጣሪ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እንዲሁም ጓደኞቼ በቅደም ተከተላቸው ሁልጊዜም ቢሆን አሉ፡፡ ወላጆቼ በሚያውቁት መጠን ጤናማ የክርስትና ሕይወትን እንድመራ ያስተማሩኝ ለእኔ ካላቸው መልካም ሃሳብ እና ዕቅድ በመነሣት መሆኑን ግን እረዳለሁ፡፡
ስሜት
ሳድግ ከትምህርት ቤት፣ ከቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከሰፈር ልጆች ጋር ጓደኝነትን መመሥረት ጀመርኩ፡፡ ልክ የጉርምስና ዕድሜዬ ላይ ስደርስ ግን ብዙ ነገሮች እየተቀየሩ መጡ፡፡ ሰውነቴ እያለፈበት ያለውን ለውጥ ለመረዳት ያን ያህል አስቸጋሪ ባይሆንም አንዳንድ ትንንሽ ነገሮች ግን “የተለየሁ” እንደ ሆንኩ እንድረዳ አድርገውኛል፡፡ ከተቃራኒ ፆታ ይልቅ ለተመሳሳይ ፆታ ተስህቦ እንዳለኝ አስተዋልኩ፡፡ ጓደኞቼ ጆሮ ለሰጣቸው ሁሉ ስለ ጉርምስና ዕድሜ ወሲባዊ ስሜቶቻቸው እና ፍላጎቶቻቸው በነፃነት ሲያወሩ እኔ ግን በእነርሱ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ አልገኝም ነበር፡፡ እኔ ለእነርሱ የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪያችን ሲያስተምር የነበረው ርጉም ነኝ፡፡ እናቴ የማይባል ነገር ስትሰማ የምትራገመው ሰይጣን ነኝ፡፡ አባቴ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን ቢሰማ በኩራት ልጄ ብሎ በጭራሽ የማይጠራኝ ልጅ ነኝ፡፡ አዎ …ጌይ ነኝ!
ለሰዎች ስለ ስሜቶቼ እና ፍላጎቶቼ፣ በቻልኩት መጠን ብሩህ ሕይወትን ለመኖር ያለኝን ፍላጎት ለመናገር አንድ እርምጃ በተራመድኩ ቁጥር እነዚህ ነገሮች የተረገሙ እንደ ሆኑ ሁሉ ወዲያውኑ ለመናገር ያለኝን ፍላጎት አቆማለሁ፡፡ አንድ የእኔን ተመሳሳይ ወንድ እንደ ወደድኩ ያመንኩ በመሰለኝ ቁጥር ፍርሃት ወደ ምድራዊ ሲኦል ይዞኝ ይወርዳል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገር አስወግዳለሁ – እዘጋለሁ፡፡ ለቤተሰቤ፣ ለጓደኞቼ ወይም ደግሞ ለእኔ አስፈላጊ ናቸው ብዬ ለነበሩት ሁሉ እዘጋለሁ፡፡ ያገኘሁት ነገር ቢኖር ኀዘንተኛ ያደረገኝን ትርጉም አልባ ጸሎት ብቻ ነበር፡፡
እርግጥ ነው በአብዛኛው የክርስትና አስተምህሮ ውስጥ ከተለመደው ፆታዊ ግንኙነት የተለየ ነገር በሙሉ የተረገመ እንደ ሆነ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ስሜቴ በሕይወት መንገዴ ላይ ብቅ በሚልበት ጊዜ ሁሉ መታገል ነበረብኝ፡፡ የኃጢአትን፣ ፆታዊ ተስህቦ እና ፆታዊ ስሜቶችን የመሳሰሉ ነገሮችን መረዳት ሁልጊዜም ቢሆን በወጣትነቴ የተቸገርኩበት ነገር ነበር፡፡ ማድረግ የቻልኩት ነገር ስሜቴን ቀብሬ ልክ እንደ ሌሎቹ ተመሳስዬ መኖር ብቻ ነበር፡፡
ፀባይ
በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ ማለፍ ለብዙ ሰው ምንም ማለት እንዳልሆነ ማስረጃ አያሻውም፡፡ ለእኔ ግን በጣም ትልቅ ነገር ነበር፡፡ አረማመዴ፣ ብርጭቆ አያያዝ እና አጠጣጤ፣ የቀለም ምርጫዬ፣ ለሕይወት ያለኝ እይታ፣ ከእግር ኳስ ይልቅ ለመረብ ኳስ ያለኝ ፍቅር፣ አኒሜተር ለመሆን ያለኝ ሕልም፣ ይህ ሁሉ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለኝን ቦታ በራሱ መንገድ ተርኮታል፡፡ ቅጽል ስሞችንም አሰጥቶኛል፡፡ በእንግሊዝኛ ክፍለ-ጊዜ አስተማሪያችን ምሳሌ የሚሰጥበት “ሴታሴቱ” ልጅ ነበርኩ፡፡ በጣም የሚያበሳጨኝ ደግሞ እንደ “ልጃገረድ” አልነበረም የሚመስለኝ፡፡ የተረገመ፡፡ የወንድ ገጸ ባሕርይን ወክዬ ለመጫወት ሙሉ ችሎታው ቢኖረኝም በአማርኛ የቲያትር ክፍለ-ጊዜ ላይ የ”እናት” ወይም “እህት” ገጸ ባሕርይ ወክዬ የምጫወተው እኔ ነበርኩ፡፡ ስፖርት አስተማሪዬ ለሌሎች ሴቶች ተማሪዎች የሚሰጠውን የተለየ እርዳታ ለእኔም ማድረግ ነበረበት፡፡ (አስደሳች ቢመስልም ይህን ተከትለው ከዛ በኋላ የመጡትን ቀልዶች ግን መቋቋም ከብዶኝ ነበር)፡፡ ይህም በትምህርት ቤት ብቻ አልተገደበም፤ በሰፈሬም ጭምር እንጂ፡፡
በአንድ በኩል ተፈጥሮ በራሷ መንገድ መሆን የፈለግሁትን መሆን የምችል መሆኔን እየነገረኝም ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በሁሉም በኩል አይደለሁም እያልኩ ተፈጥሮን እየካድኳት ነበር፡፡ ይህ ክህደት በውስጤ ያለውን ከራሴ ጋር የማደርገውን ትግል ጨቁኜ የምይዝበት ብቸኛው መንገድ ነበር፡፡ ስለ ተመሳሳይ ፆታ ፍቅር እና ፆታዊ ማንነት ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ ራሴን አምኜ እስከ ተቀበልኩበት ጊዜ ድረስ ለራሴም ሆነ በእኔ ሕይወት ላይ ተፅዕኖ ለነበራቸው ሰዎች የክህደት ኑሮን ኖሬአለሁ፡፡
ወግ አጥባቂ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖተኛ ሰዎች አንድን ሰው በፈለጉት ጊዜ በማንነቱ ምክንያት ተፅዕኖ ሊያደርጉበት ኃይል ያላቸው ወይም የተሻሉ የሆኑ ይመስላቸዋል፡፡ እንዴት መቀመጥ እንዳለብን፣ እንዴት እንደምንምል፣ እንዴት መሳቅ እንዳለብን፣ እንዴት መራመድ፣ እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለብን ሁልጊዜም ይነግሩናል፡፡ የወንዶችና የሴቶች ሚና በተለመደው ወንድ-ሠራሽ የኅብረተሰብ መዋቅር ውስጥ ባለው የተለመደ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ተቀርጿል፡፡
አንድ ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት ባስቀመጡት መስፈርት ውስጥ ምንም ዓይነት ቦታ እንደሌለኝ ተረዳሁ፡፡ ስለዚህ በባህላቸው ውስጥ ተካትቼ ለመኖር ራሴን ማስተካከል ነበረብኝ፡፡ አስቸጋሪና የሚያሳምም ነበር፡፡
የራስ ማንነት
26-ዓመት ሲሞላኝ ነበር ራሴን በማንነቴ ለመቀበል የወሰንኩት፡፡ ለራሴ መዋሸትን ማቆም እንዳለብኝ በተገነዘብሁ ጊዜ፤ ፍርሃቴን መጋፈጥ ነበረብኝ፡፡ በዚያን ወቅት ለራሴ ትንሽ የእረፍት ጊዜን በመመደብ በሕይወቴ ውስጥ ያሉኝን አማራጮች በደንብ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ በጣም ብዙ ሥነ ልቦናዊ ስቃይ ሕይወቴ ላይ ጥያቄ እንዳነሣ አድርጎኛል፡፡ ሕይወቴ ምንድን ነበር? ለራሴ እውነተኛና ፍትሐዊ በምሆንበት ጊዜ ለተስፋ መቁረጤ መልሶች ማግኘት ጀመርኩ፡፡
ራስን መቀበል በሕይወቴ ላይ የነበሩኝን ችግሮች ሁሉ የፈታልኝ ምርጡ መልስ ነበር፡፡ ያኔ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ጌይ እንደ ሆንኩ ለራሴ የነገርኩት፡፡ ጥሩ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ የራሴን ዕድል ራሴ እንድወስን በእርግጥም ቁርጠኝነት ተሰማኝ፡፡ የሚሰማኝን ሕይወት መኖሩ በራሱ ምቾት ነበረው፡፡ ኩሩ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ!
ጌይ፣ ሌዝቢያን፣ ባይሴክሹዋል፣ ትራንስጀንደር … ወዘተ. መሆን የማንነት ግጭት ወይም የሞራል ዝቅጠት አይደለም፡፡ ምርጫም ሆነ ተፈጥሮአዊ ክስተት ማንነት ያለ ባህል፣ ወግ እና ሃይማኖታዊ እይታዎች ተፅዕኖ አንድ ሰው ለራሱ የሚሰጠው ትርጓሜ ነው፡፡ በራስ ከመተማመን በላይ የተሻለ ምንም ነገር የለም፡፡ ራስን መቀበል ደስታን እና ፍቅርን የምናገኝበት ኃይል ነው፡፡ ሁሉም ሰው ፍቅርን እና ደስታን ለማግኘት የሞራልም ሆነ የሰብአዊ መብት እንዳለው አምናለሁ፡፡
ያልታወቀ 2
የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ቀጫጭን እግሮቼ በሰፊው የትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ከመሮጥ ውጪ ወደምወደው ሰው ደጃፍ ለመሮጥ ገና ዝግጁ አልነበሩም። ሰባተኛ ክፍል ነበርኩ በዚህ ዕድሜዬ። መምህራኑ ከሚያዘንቡት የእውቀት ዶፍ ውጪ የሚዘንብ የፍቅር ወለላ መኖሩን ለማወቅ አእምሮዬም፣ ልቤም ዝግጁ አልነበረም። ሰባተኛ ኤፍ፣ በግራ በኩል፣ ጥግ ላይ ከፊት ነበር የምቀመጠው። በእርግጥ ከሴቶች መካከል እቀመጥ እንደ ነበር ትዝ ይለኛል። ይህ ለምን እንደ ሆነ ግን አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው።
አንድ አጭር ፀጉረ ሉጫ ልጅ ደግሞ በመካከለኛው ረድፍ ከፊት ይቀመጣል። ሲስቅ የሚቅጨለጨል ድምፅ አለው። ጉንጮቹ ይሰረጉዱለታል። ጠጉሩ ግንባሩ ላይ ድፍት የሚል መልከ መልካም ነው።
የትምህርት ቀናቶች እየገፉ ሲሔዱ እርሱን ማየት ከትምህርት ዓይነቶቹ አንዱ ይመስል የዕለት ተዕለት ሥራዬ ሆነ። እንዲሁ እርሱን ማየት ደስ ይለኛል። ምክንያትህ ምንድን ነው ብለው በጥያቄ ወጥረው ቢይዙኝ በወቅቱ መልስ አልነበረኝም። በአንድ ክፍል ከመማር ውጪም ወዳጆች አይደለንም። እርሱም ለእኔ ቁብ የለውም። እኔም አብሬው ለመሆን ወይንም ለማዋራት ሞክሬም አላውቅም። እንዲህ እያለ ዓመቱን አጠናቅቀን ትምህርት ተዘጋና ሁላችንም በየቤታችን ተከተትን።
የዛን ዓመት ቤት የተከተተው በድን አካሌ እንጂ ልቤ ትምህርት ቤት ቀርቶ ነበር። በእርግጥ ልቤ ትምህርት ቤቱን አሥሬ የሚያስበው የቀለም ቀንድ መሆን ፈልጌ፣ አለያም የወደፊት እጣ ፈንታዬ በትምህርት በኩል መጻፉ ታይቶኝ አልነበረም። ያንን መልከ መልካም ልጅ ማግኘትና ከእርሱ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ማሳለፍ ብቻ ነበር ምኞቴ። ለምን? አላውቅም። የሐምሌ ደመና እስከነዝናቡ ጥርግርግ ብሎ ሲሔድና ነሐሴ አንድ ሲል ግን ቤት እየጎተትኩ ያስገባሁትን አካሌን ይዤ በአቅራቢያችን ወደሚገኝ ሰፈር አመራሁ። ወቅቱ እስከ ነሐሴ 16 ድረስ የሚጾምበት ወቅት ስለ ነበር እርሱ ሰፈር ወደሚገኘው ደብር በመመላለስ ማስቀደስ ያዝኩኝ። አንገቴ ላይ እራፊ ነጠላ ጠምጥሜ በቤተ ክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ ተገኝቼ፣ ዓይኔን ወዲያ ወዲህ አማትራለሁ። የክፍሌን ጓደኛ፣ ልቤ አጥብቆ ያሻውን ልጅ ግን ላገኘው አልቻልኩም። ከዚያ ይልቅ የትምህርት ቤት ጓደኞቼን አግኝቼ ስለ እርሱ መጠየቅ ቻልኩ። ያ ለማየት የጓጓሁለትና ናፍቆት እግር ተወርች አስሮ ባሪያው ያደረገኝ ልጅ ከማስቀድስበት ቤተ ክርስቲያን በቅርብ ርቀት እንደሚኖር ማወቅ ቻልኩ። ከዚያም አየሁት፥ የተራበው ዓይኔ ጠገበ።
እንግዲህ በዚህ ዕድሜዬ በፍቅር መንበር ስር ነፍሴን ማሳደር መቻሌን አላወቅሁም። ከዚያም ወዲህ ለምን ለይቼ ወንድ ልጅ ፍቅር ወስጥ ራሴን እንደምማግድ አስቤው አላውቅም። እኔ ራሴን ስበይን ወንድ ነኝ ብልም፣ የአካል ብልቶቼም ይህንን ቢመሰክሩም፣ ስሜቴ ግን ለምን ለተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እንደሚሸፍት ማሰብ አልጀመርኩም።
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አንድ አብሮኝ የሚቀመጥ የክፍል ጓደኛዬ ጋር ክፉኛ ተቀራረብን። ከትምህርት ቤት ውጪ አብረን ማሳለፍ ጠና ሲልም አብረን ማደር ጀመርን። ይህ ግን በልቤ ውስጥ የሌለ ፍላጎትን ወደ መቆስቆስ ይደርሳል ብዬ አስቤ አልነበረም።
አንድ ቀን አሁን በምን አጋጣሚ እንደ ሆነ በማላስታውሰው ሁኔታ እኔና ይህ ወዳጄ ከንፈራችን ተጣበቀ። በወቅቱ እርሱ ጢም አቀምቅሞ ስለነበር የጎረሰኝ ከንፈሩ ሙቀት ብቻ ሳይሆን የጢሙ ሻካራ ጠጉሮች ሳይቀሩ ስሜቴን አነዘሩት። ሳላውቀው፣ የእርሱን አላውቅም፣ እጆቼ ገላው ላይ መርመስመስ ጀመሩ። ትንፋሹ እየፈጠነ፣ ልቤ እየቀለጠ፣ ብልቱ እየገፋኝ፣ ብልቴ እየረጠበ ተሳሳምን። እጁን ወደ ብልቴ ሲሰነዝር እኔ የእርሱን አጠና ብልት ስይዝ አንድ ሆነ። ስሜን አቆላምጦ ሲጠራው፣ የእርሱ ስም አፌ ውስጥ ሲሟማ ምን እየተከናወነ እንደ ሆነ ለማወቅ የስሜታችን ፍላት አፍታ አልሰጠንም።
ግን ትፍስሕት በመላ አካሌ መላ፤ ደስ አለኝ። ሁሌም ደጋገምነው። ትምህርታችንን እስክናጠናቅቅ ድረስ፤ 12ኛ ክፍል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንዳችን የሌላኛችንን ስሜት ለማርካት የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። ነገር ግን ስለ ሚናችን አስበን አናውቅም። ለምን የአንዳችን ብልት በሌላኛችን አፍ ውስጥ እንደ ተገኘ፣ ለምን አንዳችን ለሌላኛችን ታፋችንን ገጥመን እንደ ሰጠን ምክንያት ፈልገንለት አናውቅም። ዝም ብሎ ያለ ንግግር መዋደድ ብቻ። ነገሩ እንኳ ከመዋደድ ይዘላል።
አሥራ ሁለተኛ ክፍል ጨርሰን እርሱ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ሲሔድ፣ እኔ አዲስ አበባ ስቀር፣ የእርሱን ባላውቅም እኔ ግን ልቤ ሌላ ከጀለ። ዳግም ፍቅር ያዘኝ፣ ማቀቅሁ። ከዚህ በኋላ ነው እኔ ለምንድን ነው ለወንዶች ብቻ ስሜት የኖረኝ? ስል የጠየቅሁት። ከዚህ በኋላ ነው ተንበርክኬ ለፈጣሪዬ ያለቀስኩት። ከዚህ በኋላ ነው ወሲብ ከፈጸምኩ በኋላ ራሴን መርገም የጀመርኩት። ከዚህ በኋላ ነው ሚናዬን መለየት የጀመርኩት። እጅግ ከረፈደም ቢሆን እኔ ማነኝ ለሚለው መልስ ያገኘሁት ብዙ ከወደድኩ፣ ብዙ ከታመምኩ እና ብዙ ከተዋሰብኩ በኋላ ነው።
የ MINTE ታሪክ
ታሪኬን ለመጻፍ ስሞክር ይህ ሦስተኛ ጊዜዬ ነው፡፡ እመኑኝ፣ የሚያስደስት ረጅም ታሪክ ስላለኝ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ውስጥ ከሚኖር መካከለኛ ደረጃ ያለው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ የተወለድሁ መደበኛ ሰው ነኝ፡፡ ሳድግ ሁልጊዜም ቢሆን የተስተካከለና የተመቻቸ ሕይወት እንደሚኖረኝ አስብ ነበር፡፡ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፤ በሕይወት የተሻለ ደረጃ እንድንደርስ ማንኛውንም ነገር ከመሠዋት ወደ ኋላ የማይሉ ወላጆች ያሉበት በፍቅር የተሞላ ቤት አለኝ፤ እናም በሕይወት ውስጥ የሚመራኝ ፈጣሪ አለኝ፡፡ ወደፊት የሚኖረኝም የተስተካከለ ሕይወት፣ በአስተማማኝ ሥራ፤ ፈጣሪን በምትፈራ ሚስት እና በደስተኛ ልጆች የተሞላ እንደሚሆን አምን ነበር፡፡ ይህ ነበር ስለ ወደፊቱ የነበረኝ እይታ እና ጠንክሬ ሠርቼ እንዲኖረኝ የምፈልገው ሕይወት፡፡
ነገር ግን ሕይወት ለእኔ የራሷ የሆነ ዕቅድ ነበራት፡፡ ዕድሜዬ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ሁሉም ጓደኞቼ ያስደስታቸው የነበሩ ነገሮች እንደማያስደስቱኝ መረዳት ጀመርኩ፡፡ በጊዜው ወንዶች ልጆች ስለ ሴቶች፣ ሴቶቹ ደግሞ ስለ ወንዶች ልጆች ያወሩ ነበር፡፡ እኔ ግን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ እኔን ጨምሮ ሁሉም ሰው “የቤተ ክርስቲያን ልጅ” ስለ ነበርኩ እንዲሁም ባለ መልካም ሥነ ምግባር እና “ጨዋ” የምባል ቻይነት ልጅ ስለ ነበርኩ እንደ ሆነ መስሎኝ ነበር፡፡ እዚህ ጋር እንዳላስት፡ እነዚህን ነገሮች ነበርኩ ፡ አሁንም ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
ነገር ግን ሴቶች ልጆችም ምንም ዓይነት ፆታዊ ተጽእኖ በእኔ ላይ አልነበራቸውም፡፡ በምትኩ ወደ ወንዶች ልጆች እሳብ ነበር፡፡ በወቅቱ ራሴን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ (ጌይ) ነኝ ብዬ መጥራት ባልደፍርም “ይህ ስሜት ምንድን ነው?” የሚሉ ዓይነት ብዙ ጥያቄዎች ግን ነበሩኝ፡፡ ምን ስህተት ተፈጥሮ ይህ ነገር እኔ ላይ ተከሰተ? እግዚአብሔር ይህ ነገር እንዲከሰት ለምን ፈቀደ? እናም በየቀኑ በጸሎትና በለቅሶ ከእኔ እንዲርቅ ብለምነውስ ለምን እምቢ አለ? እኔ ብቻ ነኝ?
ለምን በብርቱ እንደማለቅስ ወይም ከቤት እንደማልወጣ ማንም አያውቅም፤ ስለማፍርና በድብርት ስለ ተጠቃሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ያደግሁት ድክመቴን እንዳላሳይ
እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረኝን መልካም ገጽታ ይዤ እንድቆይ ስለ ነበረ እኔም ያንን አደረግሁ፡፡ ግን ከማኅበረሰቡ “ፍጹም” እና “መደበኛ” ነገሮች ራቅሁኝ ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን በኅብረተሰቡ ሞራ ተቀባይነት ከሌላቸው ነገሮች በሙሉ የከፋ እንደ ሆነ ይታመን ነበረና፡፡ በሌላ አገላለጽ ቤተሰቦቼ ጌይ ከምሆን አንድን ሰው ብገድል ብዙም አያፍሩብኝም፡፡ በጭንቀት ውስጥ የነበርኩ ቢሆንም የሚሰማኝ ነገር ምን እንደ ነበረ እንድረዳው የሚረዳኝ ሰው ግን አልነበረኝም፡፡ ስለዚህ ሕይወቴን ጠላሁት፡፡
አንድ ጊዜ ለወንድሜ “ከዚህ በኋላ የምኖረውን ሕይወት ለሆነ ሰው መስጠት ብችል በተሻለ እና በደስታ ሊኖረው ለሚችል ሰው እሰጠው ነበር፡፡” ያልኩት ትዝ ይለኛል፡፡ በወቅቱ 17 ዓመቴ ነበር፡፡ በወግ አጥባቂ እና ለመፍረድ ችኩል የሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር ራሴን እንድረዳ እና እንድቀበለው በጣም አስቸጋሪ አድርጎብኝ ነበር፡፡
ሁሉም ሰው ከእኔ የሚጠብቀው ነገር ነበር፡፡ እኔም ሁልጊዜ የሚጠበቅብኝን ነገር እያሟላሁ ኖሬአለሁ ወይም ለመኖር ሞክሬአለሁ፡፡ የራሴን እውነተኛ ማንነት ክጄ፣ ጠልቼ እና ተጠይፌው ነበር፡፡
ነገር ግን ይህ እንደማያዋጣኝ ከራሴ ጋርም ሰላም መፍጠር እንዳለብኝ ተረድቼ ነበር፡፡ ስለ ሆነም ራሴን ለማዳመጥ እና ውስጤን ለመመልከት ሞከርኩ፡፡ ምን እንደምፈልግ እና የት ቦታ እንደምፈልገው ባላውቅም ኋላ ላይ ግን አገኘሁት፡፡ መጀመሪያ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለብኝ ነበር፣ ወይም ደግሞ ይህ ነገር እንዲከሰትብኝ ያጠፋሁት ምንም ዓይነት ጥፋት እንደሌለ፡፡ አሁን 24 ዓመቴ ሲሆን በጣም የተወሰኑ ሰዎች ስለ እኔ ያውቃሉ፡፡ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን ስሜት መጉዳት ስለማልፈልግ እና ገና ብዙ ላውቃቸው የሚገቡ ነገሮች ስላሉ ሕይወቴን በግልጽ ሳልደብቅ መምራት እፈራለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን አውቃለሁ፡- የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ጌይ ነኝ ፡፡
ያልታወቀ 3
ተወልጄ ያደግሁት በትንሽዬ የገጠር ከተማ ነው፡፡ የትውልድ መንዴሬ ትንሽ ከመሆኗ የተነሣ ሁሉም ሰው ይተዋወቃል፡፡ አብዛኛው ነዋሪ በክርስትና እና በጋብቻ ሰበብ ተዛምዷል ማለት ይቻላል፡፡ ለቤተሰቦቼ የመጨረሻ ልጅ ነኝ፡፡ አባቴ ኢትዮጵያዊ አባት ነው፣ ቁጡ፡፡ እናቴም ኢትዮጵያዊ እናት ነች፣ ገራገር, የዋህ እና ደግ፡፡ ከኔ በላይ ከምንም እና ከማንም አስበልጨ የምወዳቸው ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም አለኝ፡፡ የቤቱ ድምቀት እና ዓይን ማረፊያ ነበርኩ፡፡
ልጅ ነኝ፣ ኢትዮጵያዊ ልጅ ወላጆቹን የሚወድ, አባቱን የሚፈራና የሚያከብር፣ የራሱን ሕልም ትቶ አባቱን እና ቤተሰቡን የሚረዳና የሚንከባከብ ልጅ፡፡ ወንድም ነኝ፣ ወንድም እህቶቹን የሚወድ, በተቻለው ሁሉ ሁልጊዜ ከጎናቸው የሚቆም ታናሽ ወንድም ነገር ግን የታላቅ ወንድም ያህል አሳቢ፡፡ እህቶቼ ሁልጊዜ “ማነው ግን ታላቅ?” ይሉኛል፡፡
ጓደኛ ነኝ፣ ሁሌም ለጓደኞቹ ቀድሞ የሚደርስ፣ በችግራቸውም ሆነ በደስታቸው ከጎናቸው የሚቆም፡፡ መጋራትን, መካፈልን, መደጋገፍን, መረዳዳትን የሚወድ የልብ ወዳጅ፡፡
ታዲያ በዚህ ሁሉ ውስጥ እኔ ሁለት ነኝ፡፡ አንደኛው እኔ ተጫዋቹ, ሰው አክባሪው, ደስተኛው, በጨለመ ሰዓት ሳይቀር ለሰው ብርሃን የምሰጠው, ጨዋታና ወግ አዋቂው እኔ፡፡
ሌላው እኔ ደግሞ ብቸኛው, ተስፋ የቆረጠው, በጨለማ የሚጓዘው, ከራሱ ጋር የተጣላው እኔ፡፡ በራስ መተማመኑ ከዜሮ በታች የወረደው, ብቸኝነቱን አብዝቶ የሚወደው እኔ፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪው እኔ፡፡
አዎ፣ ዓይን እና ጆሮ ያለው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪው እኔ፡፡ የምወዳቸው ወላጆቼ, ወዳጆቼ, እህቶቼ, ጓደኞቼ አጠገባቸው ቁጭ አድርገውኝ “እነሱን መግደል ነው, ማቃጠል ነው” ሲሉኝ የኖርኩ “እነሱን” የሆንኩ እኔ ነኝ፡፡ ውስጤን በማያውቁት ሰዎች መሀል ተከብቤ, በማያቸው ግን በማያዩኝ, በምሰማቸው ግን በማይሰሙኝ, የውስጤን ጩኸት ባልተረዱኝ ወላጆቼ, ዘመዶቼ እና ጓደኞቼ እየተረገምኩ እና እየተወገዝኩ የምኖረው እኔ፡፡
ልዩ መሆኔን ያወቅሁት ገና በልጅነቴ ነበር፡፡ ለማን ምን ብዬ እንደምነግረው ግራ የሆነብኝ ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ ገና በልጅነቴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ሳልሻገር ነበር ከእኩዮቼ የተለየ የማፍቀር ዝንባሌ እንዳለኝ የተገነዘብኩት፡፡ ከእኩዮቼ በተለየ መልኩ ለተቃራኒ ፆታ ሳይሆን ለተመሳሳይ ፆታ ነው ፍቅር ያለኝ፡፡ ካደግሁበት እምነት እና ባህል ያፈነገጠ ዝንባሌ ያለኝ መሆኑን በዛ በለጋ እድሜዬ ተረድቼው ነበር፡፡
ከዚህ ስሜት ለመውጣት ምን ማድረግ እንዳለብኝና ማንን ማማከር እንደ ነበረብኝ የማውቀውም ሆነ የማውቅበት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበረኝም፤ የተኰነንሁ, የተረገምሁ, የተጠላሁ እና የተገፋሁ እንደ ሆንኩ ብቻ ነበር የሚገባኝ፡፡
እርግማን ነው፣ የአምላክ ቁጣ ነው ሲሉ ሰምቼ ቤተ ክርስቲያን መሔድና አምላኬን መለመን, ፀበል መጠጣትና እምነት መቀባት አዘወተርኩ፣ ነገር ግን መሽቶ ሲነጋ…… ያው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪው እኔ ነኝ ያለሁት፡፡ ከብዙ ምሽቶች እና ንጋቶች በኋላ…. ሌላ አምላክ, ሌላ አምልኮ ሌላ ፈዋሽ አለ ሲባል ሰማሁ እናም የprotestant ቤተ ክርስቲያን መሔድ ጀመርኩ፡፡ ለፓስተሩ “ጉዴን” ነግሬው ተጸለየልኝ፣ የተጸለየበት ዘይት ተቀባሁ…… የጠዋት ፀሐይ ስትወጣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪው እኔ ነኝ ከእንቅልፌ የምነቃው፡፡ አምላኬን አምርሬ ተጣላሁት፤ እርሱም ሳይወደኝ በሚጸየፈኝ እና በማይፈልገኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ስለ ፈጠረኝ “ለምን?” አልኩት፡፡
እርሱ ሳይፈልገኝ እኔ ግን ፈልጌው ደጁን ብጠና እና ፈውስን ብለምነው ዝም ስላለኝ አብዝቼ ጠላሁት፤ አምላኬን ስጠላው ራሴንም ጠላሁት፡፡ የመኖር ትርጉሙ ጠፍቶብኝ ሕይወት እጅ-እጅ አለኝ፡፡ ከዚህ ሁሉ መገላገያ ብቸኛው ማምለጫ መንገድ ራሴን ማጥፋትና እፎይ ማለት ቤተሰቦቼንም ከሃፍረት መታደግ መሰለኝ፡፡ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ይህ ሀሳብ በአእምሮዬ ቢመላለስም ወስኜ ሕይወቴን በገዛ እጄ ለማጥፋት ግን ወኔ አነሰኝ፡፡ ለዚህም የማልሆን ከንቱ ፍጥረት ነኝ አልኩት እራሴን፡፡ እንዳልፈለግ እና እንዳልወደድ ሆኜ ወደዚች ምድር ብመጣም ራሴን ማጥፋት የሚያስችል አንድ ነጠላ ምክንያት ራሴ ላይ አጣሁ፡፡
ያኔ ነው ችግሩ ከኔ እንዳልሆነ የገባኝ፤ ያኔ ነው ስህተት አለመሆኔን ያወቅሁት፡፡ ያኔ ነው በጥላቻ ውስጥ ተጸንሼ, በጥላቻ ውስጥ ተወልጄ, በጥላቻ ውስጥ ባድግም የጥላቻው ምክንያት እኔ አለመሆኔን ለራሴ አስረግጬ የነገርኩት፡፡ ያኔ ነው ለኔ ከእኔ ውጪ ማንም እንደሌለኝ እና እራሴን እስከ ጥግ መውደድ እንዳለብኝ ያመንኩት፡፡
አሁን አድጌአለሁ፡፡ ለራሴ ጊዜ ሰጥቼ ከራሴ ጋር ማውራት ማሰብና ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ራሴን ማኅበረሰቡ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች መጠየቅና መመለስ ጀመርኩ፡፡ እውነት እኔ እንደሚባለው የምዕራባውያኑ መጤ ባህል ውጤት ነኝ? ኧረ በፍጹም! ትውልዴም ሆነ እድገቴ በጣም ገጠራማ በሚባለው የሀገሪቱ ክፍል ነው፡፡ በልጅነቴ ተደፍሬ ነበር? በጭራሽ!
የወላጅ ፍቅር አጥቼ ነበር? ኧረ እንዲያውም! በእናትና አባት, በእህትና በወንድም ፍቅር ተከብቤ ነው ያደግሁት፡፡ ከዚህ ሁሉ ፍርድና ድምዳሜ ውጪ መሆኔን አወቅሁ፡፡
እኔ ማን ነኝ? ብቻዬን ነኝ ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎቼን ለመመለስ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ጥያቄዎቼን ለመመለስ የሚረዳኝ በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ እኔን በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ ምንም ዓይነት የማነበው፣ የምሰማው ወይም የማየው ነገር ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ተስፋ ሳልቆርጥ የመረጃ መረብ (internet) አሰሳ በማድረግ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ብቻዬን እንዳልሆንኩ እና በዓለም ላይ እኔን የሚመስሉ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እህትና ወንድሞች እንዳሉኝ ሳውቅ እፎይ አልኩ፣ ከተወሰኑትም ጋር በተለያዩ መንገዶች ማውራት ቻልኩ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በሀገራችን ከሚገኙ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እህቶቼና ወንድሞቼ ጋር ማውራትና መገናኘት ቻልኩ፡፡ ይሄኔ ነው ያለፈውን ጊዜ ምን ያህል በዕውር ድንብር ስጓዝ እንደ ነበር የተረዳሁት፡፡ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ምሁራን እና የሚዲያ ሰዎች ምን ያህል ጥላቻን እየሰበኩና እያስፋፉ እንደ ሆነ የገባኝ፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ “ምሁር” የምንላቸው ሰዎች ሳይቀሩ በተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ዙሪያ ያላቸው እውቀት እጅግ አናሳ ከመሆኑም በላይ ለማወቅ ያላቸውም ፍላጎት ከዜሮ በታች ነው፡፡ እውነታ ላይ ያልተመሠረተ አስተምሮህአቸው ራሳቸው ስተው ማኅበረሰቡንም አስተውታል፡፡
አሁን እኔ ማንነቴን አውቄአለሁ፡፡ እርግማን እንዳልሆንኩ እና በፈጣሪ የተገፋሁ እንዳልሆንኩ ነጋሪ አያሻኝም፡፡ ማንነቴን አውቄና ተቀብዬ ደስተኛም ሆኜ እየኖርኩ ነው፡፡ አሁን ጨለማው ተገፍፏል ፈገግታዬም ተመልሷል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ቢሆን እኔ ያየሁትን ብርሃን ያላዩ, ራሳቸውን ያልተቀበሉ, ከራሳቸው ጋር የተጣሉ ብዙ ቁጥር ያላቸው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እህቶችና ወንድሞች በእያንዳንዳችን ጓዳ እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከአፋችን በሚወጡ መርዛማ ቃላት ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥፍተዋል፣ አሁንም በማጥፋት ላይ ናቸው፡፡ እናያችኋለን ግን አታዩንም፣ እንሰማችኋለን ግን አትሰሙንም፡፡ ስድብህ, ዛቻህ እና ማስፈራሪያህ ማን ላይ እንደሚያርፍ አታውቀውም፡፡
እኔ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ብቻ አይደለሁም፤ ልጅ ነኝ፣ ወንድም ነኝ፣ አጎት ነኝ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ከምንም በላይ ሰው ነኝ፡፡ ዛክ፡፡
የ DINBUSHEA ታሪክ
ምንም ያህል ባጨልመው ሊሳካ በማይችል መልኩ በቀድሞ ሕይወቴ/አስተዳደጌ ላይ የፆታዊ ፍቅር ዝንባሌዬ ተጽእኖ አላሳደረብኝም በሚል እምነት የጓደኞቼን “ታሪክህን አጋራን” ግብዣ ወዲያው አልተቀበልኩም ነበር፡፡
የቀለም ትምህርት ባይኖራትም ግን ልጆቿን ተግባራቸውንና ፍላጎታቸውን በማመዛዘን ራሳቸው መወሰን እንዲችሉ በማስቻል ያሳደገች እናት፣ የሕይወትህን ጥሪ በማጎልበት ሰው የሆንህ ሰው ራስህ በራስህ መሥራት የምትችል ምርጥ እንደሆንክ እየነገርህና በፍቅር የኮተኮተ አባት ኖሮህ፣ ታላላቅ እህቶችና ወንድሞችህ በጥሩ ተምሳሌትነት የተጠሩና ጥንካሬና የሚሻሻሉ ነገሮችህን እየጠቆሙ ያጎለበቱህ ሲሆኑ የልጅነት ቤተሰባዊ ሕይወትህ እንከን የለውም፡፡
በተለምዶ የሴት ወይም የወንድ የሚባሉ ተግባራትን ሳከናውን፣ የውሎ ማሳለፊያዎች ላይ ስሳተፍ እንከን አይወጣልኝም ነበር፡፡ በደስታና በፍቅር በመሳተፌ አጀቤ የትየለሌ ነው፡፡ እንዲያው ባጭሩ በቤተሰቤ የተወደድኩ፣ በሰፈሬም በተምሳሌትነት የተጠራሁ፣ በትምህርት ቤቴ ስብስባ ካለ ከመሃል የምገኝ ነበርኩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በምከታተልበት ወቅት ነው ለፆታዊ ዝንባሌዬ ስያሜ ያገኘሁለት፡፡ ምስጋናውን ለእናቴ መስጠት የምፈልገው “መጻሕፍት ውስጥ የምትፈልጉት ነገር በጠቅላላ አለ፣ አንብቡ” የሚለው የዘወትር ምክሯ ስለ ነበር ነው፡፡
በቤተ መጻሕፍቱ የባዮሎጂ መጻሕፍት ውስጥ መሀል ፆታዊ ዝንባሌዎች መኖራቸውን ማወቄ ለጥያቄዬ እረፍት ሰጥቶታል፡፡ ከፍም ሲል በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ በኢንተርኔት አማካይነት ሰዎችን ማግኘት ችያለሁ፡፡ ለዚያውም መርጬ፡፡ ለቤተሰቦቼ ባይሆን ለጓደኞቼ፣ ለአብሮ ነዋሪዎቼ ማንነቴን በግልጽ ዜጋ መሆኔን ተናግሬአለሁ፤ አልደነገጡም፡፡ ማንም ካገኘኝ በሁለትና ሦስት ደቂቃ ማወቅ ይችላል፤ ራሴን አልገድብም፡፡ በዚህም አንዳች ዓይነት ጥቃት አልደረሰብኝም፡፡ ለራሴ ቅድሚያ የምሰጥ፣ የምፈልገውን በግልጽ የማሳውቅ፣ ራሴን ለመሆን ይቅርታ የምጠይቅ አይደለሁም፡፡ ለአምስትና ለስምንት ዓመታት የቆዩ የፍቅር ግንኙነቶቼ ሁሌም እስካሁን ያስደስቱኛል፡፡ ግን ይህ ብቻ በቂ ነው? ሕይወቴ ሙሉ በደስታ የተሞላ ነው የሚለውን መሠረት ሳስበው ታዲያ ለምን በዚህ ጽሑፍ ተሳተፍኩ ብዬ አሰብኩ፡፡
የብዙዎችን ዜጎች ታሪክ በሰማሁ መጠን ነው ሕይወቴ በደስታ የተሞላች እንደ ሆነ ማሰብ የጀመርኩት፡፡ ይሄ ሴታሴት ከማለት ይልቅ ልጃችን ወይም ወንድማችን ነፃ የሆነ ሰው ነው ማለት ይመርጡ ነበር፡፡ የሰዶምና ጎሞራ ታሪክ ተነሥቶ ቢወገዝም ቅጣትን የሚሰጥ ፈጣሪ እንደ ሆነ ተሰምሮበት ነው፡፡ በየሚድያው የሚነሣው አሉታዊ የዜግነት መረጃዎች ቢዘገንናቸውም መረጃ ሳይኖራቸው መጥላትና መውደድ ያለ ምክንያት ጽዩፍ መሆኑን በማሰብ ረጅም አይሔዱበትም፡፡ ሆኖም የኔ ልዩ መሆን፣ ለምን ለኔ ብቻ ቢያውቁ የሚኖራቸው ስሜት ምን ይሆን የሚለው ሳያሳስበኝ አላለፈም፡፡ በንባብና ተጨንቄ ምንም ባለማምጣቴ ለምጄዋለሁ፡፡ ኃጢአቱንና ነውሩን ሳይነግሩኝ ቢያሳድጉኝ ግን ማንነቴን በሙሉ አሳውቄአቸው የልጅነት ሕይወቴን ማጣፈጥ እችል ነበር፡፡
ፍቅር ከተነፈገ ቤተሰብ ብገኝ፣ በልጅነቴ ብደፈር፣ በተፅዕኖ ባድግና የማኅበረሰቡን አሉታዊ ጎን ማስታረቂያ የለኝም፡፡ በፆታዊ ዝንባሌዬ ምክንያት ቤተሰብ ቢያገልለኝ፣ ተጽእኖ ፈጥሮብኝ ወደ ሱስና አላስፈላጊ የሕይወት ጎዳና ቢወስደኝ፣ ዓይናፋርና ቀለስላሳ ብሆን፣ የፆታዊ ዝንባሌ ማንነቴ የሙሉ እኔነቴ መገለጫ ባደርገው የምዛመዳቸው ሰዎች ይጨምራሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ ጫማ ያለ ካልሲ፣ ቀበቶ ሳይኖር በስኪኒ ጂንስ ተወጥሮ፣ ተንጠልጣይ ቲሸርት አድርጎና ሽቶ ተቀብቶ በጆሮ ጌጥ አብዶ፣ ሰበር-ሰካ የሚል ዜጋ በሚጠብቅ ማኅበረሰብ ውስጥ በሰላም ኖሬአለሁ፡፡ ከመሰል ጓደኞቼም ጋር ከማኅበረሰቡ መሸሸጊያ አማራጭ ነው ብለው ያመኑትን ወዳጆቻችንን ከሴት እያጋባን፣ በጭንቀት ራሳቸውን የሚያጠፉና ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡትን አብረን እየቀበርን፣ ሰው ሳይሆን ጭራቅ አድርገው የሣሉትን የዜጋ ሰው ሥዕል አይተን እነርሱ ሲዝቱ እኛ በእነርሱ እየተሳለቅን፣ የደከሙትን እያበረታን፣ አግድም የሔዱትን እየገሠጽን አለን፡፡ ለዛሬም ራሴን በዚህ መልኩ እንዳይና እንድደመም የጋበዘኝን በማመስገንና ሌሎች መሰል ዜጎችም ታሪካቸውን እንዲያጋሩ እጋብዛለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት ራሳቸውን ያዘጋጁ የተቃራኒ ፆታ ወዳጆችን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡
ድንቡሼ ገላ ነኝ፡፡
ያልታወቀ 4
ስለ ራሴ፣ ስለ ማንነቴ በልጅነት ዕድሜዬ ብረዳም ራሴን እየዋሸሁት ብዙ ቆይቻለሁ፡፡ በጊዜ ሒደት እለወጣለሁ በሚል እሳቤም ከተለያዩ ወንዶች ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ለወንዶች ምንም ዓይነት ተስህቦ የሌለኝ ችግሩ ከእኔ መስሎኝ ከተለያዩ ወንዶች ጋር አንሶላ ተጋፍፌአለሁ፡፡ ሌሎች እኔን የመሰሉ ሴቶች ተዋውቄም ይኖራሉ ብዬም አስቤም አላውቅም ነበረና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነቴን (ሌዝቢያን መሆኔን) መቀበል በጣም ከባድ ነበር፡፡ ስለ ጉዳዩም የማውቅበት ምንም ዓይነት መንገድም ሆነ ትምህርት አልነበረኝም፡፡ ኢትዮጵያ እና ባህሎቿ እንዲሁም ሃይማኖት ማንነቴን በጣም አስፈሪና ድብቅ እንዲሆን አስገድደውኝ ነበር፡፡ በዓመታት ውስጥ ግን ስለ ፆታዊ ተስህቦ ማንበብ ስለ ማንነቴም በደንብ መረዳት ጀመርኩ፡፡ ዓለም ስለ እኔ እና ስለ ማንነቴ መቼም ላያውቅ ቢችልም እኔ እና ራሴ ግን ዛሬ ባለኝ ማንነቴ በጣም ደስተኛ ነን፡፡
የ JAMES ታሪክ
ጀምስ ባላገሩ እባላለሁ፡፡ 35 ዓመቴ ሲሆን ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ አያት አካባቢ ነው:: ለቤተሰቦቼ 6ኛ ልጅ ስሆን ቤተሰቦቼ ወግ አጥባቂ የሚባሉና በከፊል በግብርና ይተዳደሩ ነበር:: ልክ እንደ ማንኛውም የአካባቢው ሕፃናት አልፎ አልፎም ቢሆን ከብት ጠብቄ እርሻ አርሜ ነው ያደግሁት:: ከ1-12 በደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ:: ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና የመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቅሁ በኋላ በአንድ የግብርና ኮሌጅ በመምህርነት ለ5 ዓመት አገልግያለሁ:: ኮሌጁ ባመቻቸልኝ ዕድልም ሁለተኛ ዲግሪዬን ተምሬያለሁ:: ባሁኑ ወቅት በዋናነት የወተት ከብቶችን በማርባት እተዳደራለሁ፡፡ በትርፍ ሰዓት ሥራ በማስተማርም ይሁን የግብርና ማማከር እሠራለሁ::
ነገሩ ባይገባኝም እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ወደ ወንድ እሳባለሁ:: በ7 ዓመቴ ሌላ ወንድ መሳሜ እና 5ኛ ክፍል ወንድ የክፍሌን ልጅ መውደዴ አሁን ትዝ ይለኛል :: በልጅነቴ ብዙም ከቤት ስለማልርቅ ብዙ ጊዜ ሬድዮ የማዳመጥ ዕድሉ ነበረኝ :: ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን (በተለምዶ ግብረ-ሰዶማዊነት) በሬድዮ የምሰማው ሁሉም መልካም አልነበረም፡፡ በእርግጥ እኔ ራሴ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን ያወቅሁት ዩኒቨርሲቲ ስገባ ነው:: በጉርምስናዬ ወቅት ማለትም ሁለተኛ ደረጃ ስማር ከትምህርት ውጭ ብዙም ትርፍ ጊዜ አልነበረኝም ስለዚህ የሚሰማኝን ወደ ወንድ የመሳብ ስሜት የማዳምጥበት ጊዜው አልነበረኝም::
ዩኒቨርሲቲ ስገባ የ17 ዓመት ወጣት ነበርኩ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር (በተለምዶ ግብረ ሰዶማዊነት) ምንነት እውቀቱ ነበረኝ ግን እኔ መሆኔን አልገባኝም ነበር:: ያኔ ነው ጉርምስናውም ከፍ ያለው ወደ ወንዶችም መሳቡ የጨመረው፤ እኔም ራሴን በብዙ ወንዶች መሃል ያገኘሁት::
እራሴን ካወቅሁ በኋላ ግን ግራ መጋባት ውስጥ ገባሁ:: በመገናኛ ብዙኀን እና በእምነት ተቋማት ስለ ተመሳሳይ ፆታ የሚነገረው ሁሉ አሉታዊ መሆኑ ትልቅ ምስቅልቅል ውስጥ ከተተኝ :: በጊዜው ምንም ጭንቀት እና ድብርት ውስጥ ብገባም ትምህርቴን በጥሩ ውጤት ጨረስኩ::
ለ10 ዓመት ያህል በጣም አስቸጋሪ ሕይወት አሳልፌያለሁ መፍትሔ የምላቸውን ሁሉ ሞክሬያለሁ:: ጾም፣ ጸሎትና ጸበል ሞክሬያለሁ ለጊዜው ቢሆን “ተፈወስሁ“ እልና ብዙም ሳይቆይ ያው ሰው መሆኔ ይገለጥልኛል:: የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ነበርኩና የተለያዩ ትምህርቶችን በመከታተል፣ ስብከቶችን በመስማትና ጾሞችን በመጾም “ኃጢአት መንገድ” ካልኩት ሕይወቴን ለመታደግ ሞክሬያለሁ:: ለሊት ለሊት እየተነሣሁ በማልቀስ በመጸለይ አምላክ ያልኩትን ተማጽኛለሁ፡፡ በአቅራቢያ ባሉ የጸበል ስፍራዎችም ተጠምቄ ነበር፣ ሁሉም ሊረዳኝ አልቻለም እንጂ:: ይህ ራሴን እንድጠላ አድርጎኛል፤ ብዙም ጊዜ እራሴን ለማጥፋት አስቤያለሁ:: ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ በጓዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም ሳይ ደግሞ የበለጠ ተስፋ እቆርጣለሁ:: ባጠገቤ በዚህ ጉዳይ ላይ ላወያየው የምችለው ሰው አለመኖሩ ብቸኝነቱን አክብዶብኝ ነበር:: ችግሩ ደግሞ ሌላ የኔ ዓይነት ስሜት ያላቸውን ሰዎች የማግኘት ዕድሉ አልነበረኝም::
በእርግጥ በሀገራችን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን እንዳሉ ባውቅም እንዴት እና የት ላገኛቸው እንደምችል አላውቅም ነበር፤ በዚያ ላይ የመገናኛ ብዙኀን ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የሚያሰራጩት ዜና አሉታዊ (አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ፣ ሰካራም፣ በውጭ ዜጎች ተገፋፍተው ወይም ተደፍረው ወደዚህ ሕይወት የገቡ፣ HIV ያለባቸው፣ ወዘተ.) ስለ ነበረ እኔም ለማግኘት እፈራ ነበር:: እኔ በግሌ ምንም ሱስ የለብኝም፤ አብዛኛው ያገኘኋቸው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ሱሰኞች አይደሉም:: ባለ ጥሩ ምግባርና ትሑት ናቸው:: በተለያዩ የእምነት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉም አሉ::
ለመጀመሪያ ጊዜ ሌላ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ጋር የማውራት ዕድሉ የገጠመኝ በ2004 ዓ.ም. በፌስቡክ ላይ ነው፤ ማለትም በ 27 ዓመቴ ነበር ::ይህ ለኔ ትልቅ እፎይታ ነበር፡፡ ብቸኝነቴንና ድብርቴን አቅልሎልኛል :: ያኔም ቢሆን ስለ ሌሎች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የነበረኝ አመለካከት በመገናኛ ብዙኀን ተጽእኖ ምክንያት በጣም አሉታዊ ነበር:: ፌስቡክ ላይ በጣም ብዙ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ማዋራት ችያለሁ፤ በዚህም በአገራችን ብዙ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ወንዶች መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን በመገናኛ ብዙኀን ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የሚነገረው ሐሰት መሆኑን ተረድቻለሁ:: በዚህ አንጻር ፌስቡክ በአገራችን ጥቂት ለማይባል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጥሩ የመገናኛ መንገድ ከፍቷል:: የተለያዩ የማኅበራዊ የጤናና የሥነ ልቦና ችግሮቻችንን ለመወያየት እና ለመተጋገዝ መንገድ ከፍቶልናል:: ከ2005 ጀምሮ ብዛት ያላቸውን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን አግንቻለሁ፤ አብዛኞቻችን ቀላል የማይባል የሥነ ልቦና እና የማኅበራዊ ቀውሶች ያሳለፍን ነን::
መንግሥትም ይሁን በበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተመሳሳይ ፆታ ጉዳዮች ላይ ያለ መሥራት ብዙዎቻችንን ጨለማ ውስጥ አስቀርቶናል:: ብቸኛ የመረጃ ምንጮቻችን እዚህም እዚያም በማኅበራዊ ድረ ገጽ የምናገኛቸው መረጃዎች ብቻ ናቸው::
የትኛውም ግለሰብ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን አለመሆኑን ራሱ/ሷ ብቻ ነው የሚያውቀው/የምታውቀው:: የትኛውም የቤተሰባችን አባል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሊሆን ይችላል፡- አባታችን፣ እናታችን፣ ወንድም፣ እህት፣ አክስት አጎት:: ብዛት ያላቸው ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በቤተሰብ ግፊትና በነገሮች አስገዳጅነት ትዳር ይዘው የልጆች አባት ሆነው ይኖራሉ ፤ ይሁን እንጂ ከትዳር ውጭ ከሌሎች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጋር የድብቅ ግንኙነት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ:: ከዓመት በፊት የአክስቴ ልጅ (ባለ ትዳርና የ2 ልጆች አባት) የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኑን አውቄያለሁ:: እኔም ብዛት ያላቸውን ባለ ትዳር የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን አግንቼ ማዋራት ችያለሁ:: ከቤተሰብ ግፊት ባልተናነሰ ለብዙ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ፈተና የሚሆነው የወደፊት የብቸኝነት ኑሮ ፍራቻ እና የዘር መተካት ፍላጎት ነው:: እኔም ለአጭር ጊዜም ቢሆን አንድ ባለ ትዳር ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበረኝ፤ በእርግጥ ባለ ትዳር መሆኑን ሳውቅ ግንኙነታችን ተቋረጠ::
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ በዕድሜ ክልል የተወሰነ አይደለም:: አብዛኛው ሰው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጨምሮ ወደ ተመሳሳይ ፆታ መሳብን ከጉርምስና ጋር ያያይዙታል:: እውነታው ግን ይህ ተፈጥሮ እና የመላው ሕይወታችን ገጽ መሆኑ ነው::
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን የፍቅር ግንኙነት ብዙ ፈተና የተጋረጠበት ነው:: መጀመሪያ ገና ስንገናኝ ብዙ ነገሮቻችንን ደብቀን መገናኘታችን ነው:: ቤተሰብ፣ ጓደኞች ይሁን የአካባቢው ሰው ስለ ፍቅር ዝንባሌያችን ካወቀ ሊያስከትልብን የሚችለውን አደጋ በመፍራት ብዙ ነገሮቻችን ምሥጢር እንዲሆኑ እንገደዳለን:: ሲቀጥል የፍቅር ግንኙነት ብንጀምር እንኳ ከምንወደው ሰው ጋር በነፃነት አብረን ማሳለፍ የምንችልባቸው ቦታዎች ስለሌሉ የግንኙነታችንን ህልውና ይፈታተነዋል:: የትኛውም የፍቅር ግንኙነት ሊጠነክር የሚችለው በመቀራረብና አብሮ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ነው:: በፍቅር ግንኙነታችን በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና እውቅና አለማግኘቱ የወደፊቱን ግንኙነታችን ተስፋ ያሳጣዋል:: አብሮ መኖር ይሁን ትዳር ለእኛ በጣም ከባድና በማኅበረሰቡ እንደ አስነዋሪ መቁጠሩ ግንኙነታችን ግብ እንዲያጣና ዘለቄታ እንዳይኖረው ያደርገዋል:: ሌላው ደግሞ ያፈቀርነው ግለሰብ በቤተሰብ ግፊት ትዳር መሥርቶ እኔን ይተወኛል የሚል ስጋት ነው:: ነገ አጋሬ ምን ዓይነት ፈተና እንደሚገጥመውና ምን ዓይነት ውሳኔ እንደሚወስን በማይታወቅበት ሁኔታ ለጀመርነው የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ብዙ መሥዋዕትነትን መክፈልን አላስፈላጊ ያደርገዋል::
በከተማና በገጠር የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ስናይ በከተማ ብዙዎችን እናገኛለን:: አንደኛ ምክንያት ከተሞች በአንፃራዊነት ያለው ነፃነት እና ይህን ተከትሎ ሌላ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የማግኘት ዕድሉ ከፍ ያለ ይሆናል:: ይህ ማለት ግን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ገጠር የለም ማለት አይደለም::
ገጠር ላይ ብዙ ሰው (ወንድም ሆነ ሴት) በልጅነት ስለሚያገቡ የሚሰማቸውን ወደ ተመሳሳይ ፆታ የመሳብ ስሜት የማዳመጥም ሆነ የመረዳት ዕድሉ አይኖራቸውም:: በተቃራኒው ደግሞ ከተማ ላይ ያለ ግለሰብ ቶሎ የማግባት እድል የለውም ያም በዋና ሁለት ምክንያት ነው አንደኛው የገቢ ሁኔታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የከተማው ሰው የትዳር አጋሩን ራሱ ጊዜ ወስዶ ስለሚመርጥ ነው:: ይህም ስሜቱን እንዲያዳምጥ እና እንዲረዳ (ከተለያዩ ምንጮች የሚገኘው መረጃ ታክሎበት) አጋጣሚውን ያመቻችለታል::
ብዙ ሰው እኛ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ሥራ የማንሠራ አድርጎ ያስበናል:: ከከፍተኛ ባለሥልጣን እስከ ቀን ሠራተኛ፣ ከፕሮፌሰር እስካልተማረው ገበሬ፣ ከነጋዴ እስከ ወታደር፣ ከአርቲስት እስከ የሃይማኖት ሰባኪ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሊሆን ይችላል:: ልክ እንደ ማንኛውም የማኅበረሰብ አባል በየትኛውም የሥራ መስክ ተሳትፈን እንኖራለን:: ለምሳሌ እኔ የምተዳደረው በዋናነት ከብት በማርባት ነው:: አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈውም ይህንኑ በመምራት ነው:: ሠራተኛ ከሌለ ወይም ሥራ ከበዛ በረት ገብቼ ከብቶች እመግባለሁ ወተት አልባለሁ አዛባ እጠርጋለሁ:: የጉልበት ይሁን የሙያዬን ሥራ ወጥሬ እሠራለሁ::
ያልታወቀ 5
አስቂኝ ሊመስል ይችላል ፤ ነገር ግን ስለ ምንነቴ የተረዳሁት በ20ዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ አያስደስተኝም ነበርና ከወንዶች ጋር መውጣት ሁልጊዜም ቢሆን አስቸጋሪ
ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ እነጫነጫለሁ፡፡ ከዛም በጓደኞቼ አማካይነት ከአንዲት ሴት ጋር ተዋወቅሁ፡፡ በመሃላችን ጓደኝነት ብቻ ቢኖርም ሌሎች ስሜቶችም ይሰሙኝ ጀመር – ይህም አስደንግጦኝ ነበር፡፡ ምን እንደሆነ እኔ ራሴም እርግጠኛ ስላልነበርኩ ለእሷም መንገርን አልቻልኩም
ነበር፡፡ በአጭሩ እሷን መውደዴ ራሴን ለማወቅ በጣም ረድቶኛል፡፡ ጉዞው ረጅም እና አስቸጋሪ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ወጥቼ እኔን በማንነቴ የሚቀበለኝ እና ያለ ምንም ግፊት ራሴን መሆን የምችልበት ቦታ ብሔድ እመርጣለሁ፡፡
የ VICTOR ታሪክ
የተወለድኩት ካዛንቺስ አካባቢ ነው፡፡ ሁልጊዜ ከሰዎች ጋር ስናወራ ስለ ተወለድኩበት አካባቢ ከተነሣ አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜን ያሳለፍኩ ይመስላቸዋል፡፡ የሚታያቸው በ12 ዓመቱ መጠጣት የጀመረ፣ በ10 ዓመቱ ደግሞ ጎረቤት ባለች ሴተኛ አዳሪ ድንግሉ የተወሰደ ልጅ ነው፡፡
እውነታው ግን እንደዛ አልነበረም፡፡ ቤተሰቦቼ በጣም ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ በዛ ላይ አባቴ የውትድርና ልምድ ስላለው የጥብቅ ሥነ ሥርዓት አራማጅ ነው፡፡ እኔንም ሆነ እህትና ወንድሞቼን ምግብ እንዴት በሥርዓት መመገብ እንዳለብን፣ እንዴት መቀመጥ እንዳለብን እንዲሁም አልጋችንን እንዴት በወታደራዊ ሥርዓት ማንጠፍ እንዳለብን ያስተምረን ነበር፡፡ ሁሉም ነገር መዘርዝር ነበረው፡፡ እንግዲህ አባቴ ምን ያህል ወግ አጥባቂ እንደ ነበር አስቡት፡፡
ለቤተሰቤ በሁለት ሌሎች ልጆች መሀል የተገኘሁ ልጅ ነኝ፡፡ አንድ እህት እና ታናሽ ወንድም አሉኝ፡፡ ስናድግ ከቤት መውጣት አይፈቀድልንም ነበር፡፡ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ብቻ – ጥብቅ ቁጥጥር ያለበት እንቅስቃሴ ነበረን፡፡ እህቴ በአባቴ ታናሽ ወንድሜ ደግሞ በእናቴ የበለጠ ቢወደዱም ብቸኛ መሆንን ለምጄው ነበረና ብዙም አያስጨንቀኝም ነበር፡፡ ዓይናፋር፣ ቁጥብ እና ትሑት የምባል ዓይነት ልጅ ነበርኩ፡፡ አሥር ዓመት ሲሞላኝ ያለ አዋቂ እርዳታ ምግብ ማብሰል፣ ቤት በጥሩ ሁኔታ ማጽዳት እና ሌሎች የቤት ሥራዎችን ማከናወን ችዬ ነበር፡፡ ከወንድምና እህቴ ትንሽ ለየት ያልኩ ስለ ነበርኩ ቶሎ አድጌ ጠንካራ መሆን ነበረብኝ፡፡
ጉርምስና ላይ ስደርስ እና በእኔ እድሜ ያሉ ሌሎች ወንዶች ልጆች እንደ “ወንድ” ሲጎረምሱ እኔ ግን ገና ነበርኩ፡፡ ሴቶች ልጆች ደግሞ ሰውነታቸው እየተቀየረ ወደ ሙሉ ሴትነት ሲያድጉ ለኔ ግን ያው የማውቃቸው ትንንሽ ልጆች ነበሩ፡፡ ምንም አይስቡኝም ነበር፡፡ ወዲያው እንደ ሌሎች አብሮ አደጎቼ አለመሆኔን ባውቅም የሚከፋው ነገር ግን ብቻዬን መሆኔ ነበር፡፡ ኃፍረቱ እና የጥፋተኝነት ስሜቱ በወቅቱ ከየት እንደ መታ ባላውቅም ስሜቶቼ እና ሃሳቦቼን ግን ሁሌም ለራሴ ብቻ ነበር የማወጋው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በፍጹም ተወርቶበት ስለማይታውቅ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሼ ነበር፡፡
ዓመታት አልፈው 14 ዓመት ሞላኝ፡፡ ምሥጢሬን እና ግራ መጋባቴን መሸከም የማልችልበት ደረጃ ላይ ደረስኩ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌይ መሆኔን ተረድቼ ነበር፡፡
እንዲተወኝም እፈልግ ነበር፡፡
ከማጠቃለያ ፈተና በኋላ ያለው ረጅም እረፍት ላይ ነበርኩና ከሃሳቦቼ የሚያናጥበኝ አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ ብስጭቴ እና ግራ መጋባቴም እየጨመረ መጣ፡፡ ላቋርጠው ወሰንኩ፡፡ ወደ ቤተሰቦቼ መኝታ ቤት ገብቼ የመድኃኒት ማስቀመጫ ሣጥኑን ከፈትኩት፡፡ በውስጡ 8 ወይም 10 ዓይነት መድኃኒቶች ነበሩ፡፡ ከእያንዳንዱ ትንሽ ትንሽ አድርጌ በመውሰድ ወደ አፌ ጨመርኳቸው፡፡ ሣጥኑን እንደ ነበረ በጥንቃቄ በመዝጋት ወደ ክፍሌ በመሔድ አልጋዬ ውስጥ ገብቼ መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ 8ኛ ክፍል ነበርኩ፡፡ በፊልሞች ላይ እንደማየው አንቀጥቅጦኝ ወዲያው ፈጣን ሞት ጠብቄአለሁ፡፡
እንባዬ በጉንጮቼ ሰንጥቆ እየወረደ ጠበቅሁ፡፡ እስከሚያንቀጠቅጠኝ ድረስ በፍርሃት ጠበቅሁ፡፡ እናቴ እንዴት እንደምታለቅስ… አባቴ ግራ በመጋባት “ለምን” እያለ ሲያስብ… ይታየኝ ጀመር፡፡ ደብዳቤ ጽፌ ማስቀመጥ አልፈለግሁም… ምን ብዬ እጽፈዋለሁ? እንዴት ብዬ እገልጸዋለሁ? ከጭንቀቴ መገላገል ብቻ ነበር የፈለግሁት… ረጅም የአእምሮ ሰላም፡፡
ከሰዓታት በኋላ እህቴና ወንድሜ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ነበር የነቃሁት፡፡ ሞት እንኳ ስላልፈለገኝ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ መድኃኒቱ ምንም ዓይነት ጉዳት አላስከተለብኝም… ጥልቅ እንቅልፍ ብቻ፡፡ ከዚህ ሙከራ በኋላ የከፋው ነገር ስለ ሞት ሁለት ዓይነት ስሜቶች ተተኩብኝ፡፡ አንደኛው ሞት እስኪመጣ ድረስ ያለው የጭንቀት ሰዓት ከማስፈራቱ የተነሣ ሁለተኛ ላለመሞከር ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንዴ ከሞከርኩት በኋላ… ሞት ቀላል ነገር ነው፡፡ ከዚህ ሁነት በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድና መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
ፈጣሪ ያልገደለኝ መፍትሔ ስላለው ይሆናል ብዬም አሰብኩ፡፡ ያንን ነበር በተደጋጋሚ ለራሴ የነገርኩት፡፡ ፆታዊ ተስህቦዬ ለቤተ ክርስቲያን እና ለፈጣሪ ታማኝ በመሆን የምጋፈጠው እና የማሸንፈው ፈተና እንደ ሆነ አመንኩ፡፡ ለታላላቆቼ እንዲጸልዩልኝ እነግራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ምን እንዳስጨነቀኝ እና ለምን እንደሚጸልዩልኝ አልገልጽላቸውም፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥም በትምህርት ቤት፣ በአካባቢዬና ብሎም በኮሌጅ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር በቃሁ፡፡ ቢሆንም ላለመሸነፍ ከራሴ ጋር ብርቱ ትግል ነበረብኝ፡፡ እስካሁን እኔን የመሰለሰው አላገኘሁም፡፡ ጸለይኩ… ጠንክሬ ጸለይኩ፡፡ ከ24 ሰዓታት በላይ ፈጣሪ እንዲለውጠኝ ፆምኩ… ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡
ምንም የሚለወጥ ነገር እንደሌለ ለመረዳት የሕይወቴን ግማሽ ያህል ጊዜ ወስዶብኝ ነበር፡፡ ደህና ነበርኩ፡፡ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ማግኘት የሚገባኝን ፍቅር እና ድጋፍ ላላገኝ እችላለሁ፣ ነገር ግን አሁን የሚያስፈልገኝ ነገር ራሴን መውደድ ብቻ መሆኑን አመንኩ፡፡
ይኸው አሁን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እና ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔን በእኔነቴ… እንዳለሁ የሚወዱኝ በጣም ብዙ ጥሩ ጓደኞችን አፍርቻለሁ፡፡ ሰዎች ስለ እኔ ውሸትን ሊናገሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን አሁን እኔ ራሴን አውቃለሁ፡፡ በጭራሽ ተደፍሬ አላውቅም፣ እንኳንስ ከኢትዮጵያ ከአዲስ አበባም ወጥቼ አላውቅም ነበር፣ “ተማርክበት” ለምባለው የምዕራባውያን ባህል በወቅቱ ምንም ዓይነት ተጋላጭነት አልበረኝም፡፡ በቃ… እንዲሁ ነበር የተፈጠርኩት… ብቻዬንም አይደለሁም፡፡
ስለ እኛ እንደሚነገረው የተሳሳተ አመለካከት ያየሁትን ወንድ ሁሉ ለፍትወት አልመኝም፡፡ ካገኘሁት ወንድ ጋር ግንኙነት እንድፈጽም የሚገፋፋ ምንም ዓይነት አሳካኪ ነገር የለብኝም፡፡ ልክ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በተስህቦዬ ምክንያት በሽተኛ ወይም ስንኩል አይደለሁም፡፡ እየሠራሁ ለሀገሬ እድገት የተቻለኝን አደርጋለሁ፡፡ አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ መድረክ ሲያሸንፉ ልክ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በደስታ እጮሃለሁ፡፡ በኢትዮጵያዊ ሙዚቀኞች ሙዚቃ እና ዳንስ ደስ እሰኛለሁ፡፡ እንዲሁም የተራበን ሕፃን ወይም የተቸገረች እናትን ሳይ ደግሞ አዝናለሁ፡፡ እንደ ሁሉም ሰው ሰው ነኝ፡፡
ዳይፐር አድርጎ ይንቀሳቀሳል ሲሉ ሐሰት ነው፤ ሕፃናትን ለመመልመል ይደፍራቸዋል ሲሉም ውሸት ነው፤ “የጌይ አጀንዳ”ን ለማስፋፋት ከውጪ ሰዎች ብር ይቀበላል ሲሉም… ሐሰት! የእኛ ብቸኛ አጀንዳ የሁሉም ሰው ሊሆን እንደሚገባው ሰላም፣ ፍቅር እና ብልጽግና ነው፡፡ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥፍተዋል፡፡ ብዙዎች ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተጋብተው እውነተኛ ፍቅርን ደብቀው ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ብዙዎች የውስጥ ሕመማቸውን ለማደንዘዝ ሱሰኝነት ውስጥ ገብተዋል፤ ብዙዎች ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ በሚመሩት ጥንቃቄ አልባ ሕይወት ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
እናት ለልጇ ሕይወት መጥፋት አንዷ ምክንያት መሆኗን ሳትረዳ ታለቅሳለች፡፡ አባት “ወንድ” እንዲሆን እና ያለ ፍላጎቱ ሚስት እንዲያመጣለት ክፉኛ ገፋፍቶ ወደ መቃብሩ ለሸኘው ልጁ ኀዘን ይቀመጣል፡፡
አብረናችሁ ነን… ስለምንመስላችሁ ግን ለይታችሁ አታውቁንም፡፡
ያልታወቀ 6
አዎ! ኢትዮጵያዊ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነኝ!
ምናልባት ማን እንደ ሆንሁ፣ ስለ ማንነቴ፣ ከየት እንደ መጣሁ ወይም ምን ዓይነት ፍጥረት እንደ ሆንሁ በግርምት እያሰላሰላችሁ ከሆነ … ተረጋጉ! ከሌላ ዓለም የተገኘ ባዕድ ፍጥረት ወይም መንፈስ አይደለሁም፡፡ ከዚሁ ከመሬት የተገኘሁ “ሰው” ከሚባለው ፍጥረት ወገን ነኝ፡፡ ከሴት እና ከወንድ አብራክ የተገኘሁ … ከዘጠኝ ወር እርግዝና በኋላ የተወለድሁ… እንደ ማንኛውም ልጅ አድጌ አሁን ያለሁትን ሰው የሆንሁ፡፡ ይህ እንደ “ሰው” ወይም “የአዳም ፍጥረት” ካላስቆጠረኝ ወይም አንድ ሰው … ሰው ለመባል ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ዝርዝር ካሏችሁ፡ እንግዲያውስ ታሪኬን ልንገራችሁ፡፡
ውድ አንባቢ፣ ኢትዮጵያዊነት ልዩ መሆን እና እንደ ወርቃማ እድል የምትቆጥረው ከሆነ… እሺ፤ እኔም ከዚሁ ነኝ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልጄ ያደግሁ 100% ኩሩ ኢትዮጵያዊ፡፡ ሀገሬን እስከ ሞት የምወድ ኢትዮጵያዊ፡፡ የምወደው እና የማከብረው ወገኔ የሌለበት የሀገሬ ሰላም ያልተረጋጋበት ሕይወት ለእኔ ሕይወት አይደለም፡፡ ጉረኛ ሆኜ ወይም ድራማ ለመፍጠር ብዬ አይደለም፡፡ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ከሆነ የተማርኩ እና ደህና የሚባል የሥራ ሙያ አለኝ፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ጠንክሬ እየሠራሁ ሕዝቤን እና ሀገሬን የማገለግል ሰው ነኝ፡፡ “ጠንካራ ሠራተኛ ዜጋ” የሚል ስም ትቼ ለማለፍ እና ወደፊት የሚመጣው ትውልድ እያየ የሚማርበት አርአያ ለመሆን በትጋት እሠራለሁ፡፡
ይህም በቂ ካልሆነ እና ሃይማኖትህስ ከተባልኩ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ፤ ያውም አጥባቂ፡፡ ዘወትር እሁድ ቤተ ክርስቲያን እሔዳለሁ፣ አስተምህሮውን እቀበላለሁ፣ ቅዳሴ እከታተላለሁ በተጨማሪም እንደ ሁሉም ሰው በዓላትን አከብራለሁ እደሰትባቸዋለሁም፡፡ በሃይማኖት መኖሬ ጨዋ፣ ታዛዥ፣ ለጋስ እና ሕግ አክባሪ ትሑት ሰው እንድሆን ረድቶኛል፡፡
ለባህሉ ቅድሚያ የሚሰጥ በባህል የሚመራ ልዩ ሰብእና ያለው ከሆነ የምትፈልጉት፣ እርሱ እኔ ነኝ፡፡ እውነት ለመናገር ያለ እንጀራ እና ክትፎ ህልውናዬ አደጋ ላይ ነው፤ ሕይወትንም ከዛ ውጪ ማሰብ አልችልም፡፡ በእውነት እጠፋለሁ፡፡ “በጠጅ” እና “እስክስታ” ያልታጀበ ጨዋታ መቼም ምርጫዬ አይደለም፡፡
ቢሆንም ግን እንደ ማንኛውም ሕይወት ያለው ፍጥረት 100% ፍጹምም አይደለሁም፤ ብዙ እንከኖች አሉብኝ፡፡ አንዳንዴም ደካማ እሆናለሁ፣ ስሜታዊም ነኝ፡፡ በውጣ ውረድ ውስጥ እያለፍሁ ኖሬአለሁ፣ አሁንም እኖራለሁ፡፡ ስህተቶችን እሠራለሁ፣ ነገር ግን እማርባቸዋለሁ፡፡ ብደነቃቀፍና ብወድቅም እንደገና ተነሥቼ ጉዞዬን እቀጥላለሁ፡፡ ታምሜም እድናለሁ፡፡
ምንም እንኳ የተለመደው ሰብአዊ ፍጡር ያለው ነገር ያለኝ እና እንደ ማንኛውም ሰው የምንቀሳቀስ ብሆንም ከእናንተ እንደ አንዱ እንዳልሆንኩና ከተለመደው ወጣ ያልኩ የሆነ ችግር ያለብኝ እንደሆንኩ ታስባላችሁ፡፡ ከተለመደው በተለየ የፍቅር ግንኙነት ስላለኝ ብቻ መኖር የማይገባው ኃጢአተኛ ተደርጌ እቆጠራለሁ፡፡ አንድ ሰው ላይ ጥላቻን ማወጅ እና እንዲሞት መፍረድ ከፍተኛ ጭካኔ አይደለም ትላላችሁ? እስኪ ቆም በሉና ሕይወታችሁን ተመልከቱት፣ ከምንም ካላችሁ እና ከምታስቡት ያነስሁ እንዳልሆንኩ እሞግታችኋለሁ፡፡ ለምንድነው ግን ጭፍን ጥላቻን የምንወደው?
አዎን ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነኝ! ከተለመደው በተለየ በማፍቀሬ የመጨረሻውን ወንጀል እየፈጸምኩ ነው ማለት ነው? ለወንዶች መሸነፌ እና በፍቅር መውደቄ በሽተኛ ያደርገኛልን? ውድ አንባቢ፣ ምናልባት ከረሳችሁት አንድ እውነታ ላስታውሳችሁ፡፡ “ፆታዊ ተስህቦዬ ዘሬንም ሆነ ሰውነቴን አያጠፋውም!” አዎን አፈቅራለሁ፣ ነገር ግን ከእናንተ በተለየ፡፡ እናንተ ለተቃራኒ ፆታ ትሳባላችሁ፡፡ ለምትወዱት ሰው የሚፈልጉትን ነገር ለማድረግ የማትፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ አውቃለሁ፡፡ ለመውደድ እና ለመወደድም እንደምትተጉም አውቃለሁ፡፡ ያንንም አከብራለሁ፣ እቀናበታለሁም፡፡ እኔም በውስጤ ተመሳሳይ መንፈስ እና ፍላጎት ያለኝ እንደ እናንተው ሰው ነኝ፡፡ ለማፍቀር አልተረገምኩም፣ እንዲያውም ልክ እንደናንተ ዓይነት ስሜት አለኝ፣ እናንተ እንደምታፈቅሩት የማፈቅር በመሆኔም የተባረክሁ ነኝ፡፡ ለመውደድም ሆነ ለመወደድ እፈልጋለሁ፡፡ የፍቅር አጋርነትን በረከቶች እና መልካምነት ለመጋራት ጥሬአለሁ፡፡ ስለ ፍቅር ስናወራ አንድ ዓይነት አመለካከት እና እይታ እንዳለን አውቃለሁ፤ ጥያቄው የሚነሳው ግን ማንን እንደ ወደድን ስንጠያየቅ ብቻ ነው፡፡ ለእኔ ወንድን ማፍቀሬ ስህተት ከሆነ፣ ትክክል መሆንን አልሻም፡፡ ስህተት የሆነው በእናንተ ዓይን ብቻ ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰብእ ልዩ ፍጡር ሲሆን አንድ ዓይነት ባሕርይም የለንም፡፡ ፍቅራችን ገደብ እና ምርጫ የለውም፡፡ በተለየ ሁኔታ ስላፈቀርኩ ብቻ ስህተተኛ ወይም ማፍቀር የማልችል አይደለሁም፡፡ ወንዶችን ማፍቀሬ እና አብሬአቸው መኖሬ ከወንዶች ያነሰ ወይም ኢትዮጵያዊ አይደለህም የሚያስብል እንዳልሆነ አጥብቄ አምናለሁ፡፡ ያደግንበት እና አሁንም ድረስ የምንኖርበት ማኅበረሰብ በጣም ወግ አጥባቂ እና በጣም ብዙ ጥሩና መጥፎ ጎኖች ያሉት ነው፡፡ እናንተም የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደሆነ ከሚያስበው፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪን ወግሮ ከሚገድለው እና በሕይወት ከሚያቃጥለው፣ ገርፎ እና በድንጋይ ወግሮ ከሚገድለው፣ እንዲሁም ፍትሕ ሲጓደል ለማስቆም ከማይደፍረው ከሰፊው ማኅበረሰብ ውስጥ ብትሆኑ ብዙም አይደንቀኝም፡፡ ኃጢአተኛ ለመባል ምን ስህተት ሠራሁ? የውስጤን ድምፅ ስለ ሰማሁ፣ ልቤን ስለ ተከተልሁ እና ደስተኛ ለመሆን ስለ ጣርሁ? የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን በተረዳችሁበት ቅፅበት ምን ዓይነት እይታ እንደሚታያችሁ አውቃለሁ፡፡ አስጠላችኋለሁ፣ አይደለም? ያጥወለውላችኋልም፣ ልክ ነኝ? ሃፍረታችሁ እንደ ሆንኩም አውቃለሁ፡፡ ለእናንተ በሕይወት ውስጥ የመጨረሻው አስከፊ ኃጢአተኛ ነኝ፡፡ ኅብረተሰባችን ወንድ መሆን አለበት ብሎ የሚያስበውን ወንድ እንዳልሆንኩ እና የማያልቁ ብዙ መጥፎ ነገሮችንም ነኝ፡፡
ማርቲን ሉተር አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ከፍቅር ጋር ለመቆራኘት ወስኛለሁ፤ ጥላቻ ሊሸከሙት የማይችሉት ከባድ ሸክም ነውና፡፡” በአጉል ኩራት ስለ ፈረዳችሁብኝ እና እስከ ሞት ስለ ጠላችሁኝ እኔ እንደናንተ አይደለሁምና አልጠላችሁም፡፡ ለምን እና እንዴት እንደሆነ ብታውቁ በእርግጠኝነት ትፀፀቱበት ነበር፡፡ እውነታው “በጭራሽ ፈልጌ እና መርጬ የሆንኩትን አልሆንኩም፤ በቀላሉ እኔ እኔ ነኝ”፡፡ ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነኝ፡፡ እንደ ተወሳሰበ የሂሳብ ትምህርት ነው እንዴ? እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ምክንያቱን በማላውቀው መንገድ በዙሪያዬ ለነበሩ ወንዶች ልጆች የመሳብ ባሕርይ ነበረኝ፡፡ እወዳቸው እና እፈልጋቸው ነበር፡፡ ጓደኞቼ በተቃራኒ ፆታ ፍቅር ሲወድቁ የእኔ ግን ሌላ ነበር፤ በሽተኛ የሆንኩ መስሎኝ ፆታዊ ተስህቦዬን ለማስተካከል ብዙ ታግያለሁ፡፡ የሴት ፍቅረኛ እንዳለኝ ሚሊዮኖች ጊዜ አስመስያለሁ፡፡ ሰዎች እንደሚጠብቁኝ ለመሆን የማላሸንፈውን ጦርነት በጣም ብዙ ጊዜ በራሴ ላይ አውጃለሁ፡፡ እያንዳንዱ ቀን አስቸጋሪ ነበር፤ አሁንም ነው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳየው በብቸኝነት ያለ ምንም ጦርነቴን የሚካፈል አጋዥ እንዲሁም አብሮኝ ችግሮቼን የሚካፈል ሰው ያሳለፍኩትን ጦርነት ሳስብ እስካሁን ያስደነግጠኛል፡፡ ራሴን ብሆን የሚደርስብኝን መገለል፣ መድልዎ እና የፍትሐ መጓደል እፈራው ነበር፡፡ እስኪ እባካችሁ ለአንድ ሰከንድ ቆም በሉ እና ራሳችሁን በእኔ እግር ተኩት፡፡ አውቃለሁ ቅዠት ነው፡፡ እስካሁን ለራሴ ብቻ ይዤው ብቆይም ይኸው ዛሬ የድርሻዬን ታሪኬን እናገራለሁ፡፡ በጣም ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች እና አሉባልታዎች ስለሚበዙ ቢያንስ የራሴን እውነት ግልጽ ላደርገው እወዳለሁ፡፡
ፆታዊ ጥቃት የደረሰብኝ ወይም የተደፈርኩ ለሚመስላችሁ ለእናንተ፣ ወይም ክፉ ደፋሪ ለምታደርጉኝ ለእናንተ፣ መልሱ ልክ እንደ ሰማያዊ ሰማይ ጥርት ያለ ነው፡፡ በጭራሽ! መድፈር በየትኛውም ደረጃ ሕገ ወጥ እና ኢሰብአዊ ነው፡፡ የሚሠራ አእምሮ እና ግብረ ገብ ያለው ማንኛውም ሰው በሌሎች ላይ አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ ጥፋት ወይም አደጋ ለማድረስ አይደፍርም፡፡ ፍቅር የበላይ እና ቀዳሚ በሆነበት መልካም እና ጠባቂ ቤተሰብ እና ማኅበረሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ ከሁለት ወንድሞቼ ጋር በተወዳጅ ወላጆቼ ነው ያደግሁት፡፡ ከቤተሰቦቼ የምናገኘው ፍቅር እና እንክብካቤ ለሁላችንም በእኩል መጠን ቢሆንም ወንድሞቼ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ አይደሉም፡፡ ከሌሎቹ ባነሰ ወይም በተለየ ሁኔታ አልታየሁም፡፡ ታዲያ ሁነኛ ምክንያት አላችሁን? ሙሉ ፆታዊ ማንነቴ ወይም ተስህቦዬ በማንኛውም ዓይነት ውጫዊ ኃይል ያልተጫነብኝ አብሮኝ የተፈጠረ እና ከውስጥ የመነጨ ነው፡፡
ኃጢአተኛ እና ሰይጣን የተጠናወተህ ነህ ነው ያላችሁኝ? መጀመሪያ ጊዜ በፆታዊ ተስህቦዬ የተለየሁ መሆኔን ሳውቅ እብድ የሆንኩ እና ክፉ ሥራን የሠራሁ ነበር የመሰለኝ፡፡ ልዩ መሆኔን አምኖ ከመቀበል ይልቅ፣ አቅሜን፣ ጊዜዬን እና ሁሉ ነገሬን ፈውስ በመፈለግ እና “የተለመደ” የሚባለውን ነገር ለመሆን አቃጥያለሁ፡፡ ፍጹም ቂልነት እና እብደት ነበር፡፡ ሌት ከቀን በትጋት ጸልዬአለሁ፣ የቀናቴን ረጅም ሰዓታት በፆም አሳልፌአለሁ፣ በተጨማሪም ወደ ጸበልም ተመላልሻለሁ፡፡ ነገር ግን ምንም የሚፈይዱት ነገር አልነበረም፡፡ በጊዜ ሒደት ብቸኛ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እንዳልሆንኩ እና በእርግጥም ሚሊዮኖች እንዳሉ፣ ሌሎች ሚሊዮኖችም ተደብቀው ሕይወትን እየዋሹ እንደሚኖሩ ተረዳሁ፡፡ ውድ አንባቢዬ፣ የምጽፈው ኀዘኔታን ለማግኘት ብዬ አይደለም፡፡ በየቀኑ ሰዎች ያጋጥሙኛል፣ የውስጥን ድምፅ ክዶ የማይፈልጉትን ሕይወት ለመምራት መገደድ በእርግጥም ያማል፡፡ ነገር ግን ያልሆንኩትን ሆኜ ለመኖር አልፈልግም፡፡ ትናንትና ለጓደኛህ የነገርከው ውሸት አንተን የተሻለ ኃጢአተኛ እንደሚያደርግህ ካሰብክ ቀጥልበት፡፡ ፍረድብኝ፡፡ ከሥራ ቦታህ ያጭበረበርከው ገንዘብ የተሻለ ሰው ያደርገኛል ብለህ የምታስብ ከሆነ፣ አሁንም ፍረድብኝ፡፡ በሚስትህ ላይ መወስለት ከእኔ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነት የተሻለ እንደሆነ ካመንህ ልቀበልህና ጣት መቀሰርህን ቀጥልበት፡፡ ካልሆነ ግን የእኔን ኃጢአቶች ከአንተ ጋር ማወዳደርህን አቁም፡፡ በእውነት ላይ ተረማምደህ እየሔድክ ጥላቻህን ግን በእኔ ላይ መንዛት ከፈለግህ ይሁንልህ፣ ግን ራስህን አታልል፡፡
አሁንም በምዕራቡ ዓለም ባህል እና ፊልሞች ተፅዕኖ ስር የወደቅሁ እና ስሜቴን ከነሱ ያገኘሁት ከመሰለህ የተሳሳተ በር ላይ እያንኳኳህ እና ከተሳሳተ ሰው ጋር እያወራህ ነው ማለት ነው፡፡ ተሳስተሃል! ፈጣሪ በሚያውቀው መሠረታዊ ነገሮችን ብቻ ማሟላት ከሚችል ድሀ ከሚባል ቤተሰብ የተገኘሁ ነኝ፡፡ የተቀደደ ዩኒፎርም እና ያንን “ሰማያዊ ሸራ ጫማ” ተጫምቶ መንግሥት ትምህርት ቤት የተማረ ድሀ ልጅ ነበርኩ፡፡ ቴሌቪዥን በቤታችን አልነበረንም፡፡ በዚያን ጊዜ በጣም ተወዳጅ የሆነውን “120” የቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም ለማየት እሁድ እሁድ ወደ ጎረቤት ቤት የምሔድበትን ያንን መልካም ጊዜ አሁንም ድረስ አስታውሰዋለሁ፡፡ ትምህርት የስኬት ቁልፍ መሆኑን በማመን እና ብሩህ ተስፋ እንዲኖረኝ እንዲሁም የማልመውን ምቾት ለማግኘት ጠንክሬ ሠርቻለሁ፡፡ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከክፍሌ አንደኛ በመሆን አጠናቅቄ የወደፊት ሕይወቴን ቅርፅ ለማስያዝ እና ወደ ሕልሜ የሚያደርሰኝን ጎዳና ለመያዝ ኮሌጅ ተቀላቅያለሁ፡፡ ሕይወት በኮሌጅም ቢሆን የተለየ ታሪክ አልነበረውም፡፡ በጣም በትንሽ ገንዘብ፣ በወር 100 ብር ብቻ እየተጠቀምኩ አሳልፌአለሁ፡፡ የቴክኖሎጂን መሠረቶች ምንነት የማያውቅ ድሀ ተማሪ የነበርኩ ሲሆን ትምህርቴን ከእነዚህ በመራቅ አጠናቅቄአለሁ፡፡ ነገር ግን ከኮሌጅ ልመረቅ አካባቢ የኢሜይል አካውንት የመፍጠር ዕድሉ ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ የሞባይል ስልኬን 23 ዓመቴ ላይ ነበር የያዝኩት፡፡ ልብ ወለድ ይመስላል? ሕይወቴ እንዲህ ነበረና “በምዕራባውያኑ ፊልሞች የባለገ” የሚለውን ነገር ተወኝ፡፡ ጽንሰ ሃሳብህ ነባራዊ አይደለምና እኔ ላይም ሆነ ሌሎች በሌላ ዓይነት ፆታዊ ተስህቦ የሚኖሩ ሰዎችንም አይመለከትም፡፡
ውድ አንባቢ፣ ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነቴን ከአንስታይ ባሕርያት መኖር ጋር ወይም በቂ ተባዕታይ ባሕርይ አለመኖር ጋር አገናኝተህ “ሴታሴት” የምትለኝም ከሆነ፣ አሁንም ተሳስተሃል፡፡ የወንዳወንድነት ትርጓሜህ አሪፍ እና የሚታይ የብልት ቅርፅ ባለውም ከሆነ እኔም ተለቅ ያለ አለኝ፣ ሁኔታዬም “ወንዳወንድ” ወይም “የተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ” ዓይነት ነው፡፡ ኢንተርኔት ላይ በመግባት የወንድ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የሚገርም ውበት እና “ወንዳወንድነት” ማየት ትችላለህ፡፡ እርግጠኛ ነኝ የሚያደንቃቸውና የሚወዳቸው የሆነ የስሜትህ ክፍል አለ፡፡ እውነታውን አትካድ፡፡ ምንም ነገር በሁሉም ጊዜ አንድ ዓይነት አይደለም፤ ሁሉም ነገሮች የሆነ የተለየ ነገር አላቸው፡፡ እርግጥ ነው በትርጓሜህ የሚካተቱ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ባንተ ትርጓሜ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ብዙ የተቃራኒ ፆታ አፍቃሪያንን አውቃለሁ፡፡ ይህን እንዴት ትገልጠዋለህ? ወንዳወንድነት እና ሴታሴትነት ከቆዳ ጥልቀት በላይ ናቸው፡፡ እኔም ከማውቀውና ከምረዳው በላይ ነውና እሱን ለባለሙያዎቹ እተወዋለሁ፡፡
አዎ! እውነታው እንደ ማንኛውም ሰው ነገር ግን የተለየ ተስህቦ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ የሕይወቴን እያንዳንዱን ክፍል በደስታ ማሳለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ሰላማዊ እና ተግባቢ ነኝ፡፡ ነገር ግን ያንተ የተሳሳተ ፍርድ ሕይወቴን በስቃይ እና መከራ እንድመራ አድርጎኛል፡፡ ራሴን በኩራት ከመቀበል ይልቅ በድራማ እና በጥፋተኝነት ስሜት እንድኖር አስገድዶኛል፡፡ በእኔ ቦታ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? አንድ ሰው እንዴት በንጹሕ ፍጥረት ላይ የሞት ፍርድ ይፈርዳል? ቤተሰቦቼ ስለ ትዳር እና ስለ አማቻቸው ሲጠይቁኝ ምን ልበል? ስለ ፆታዊ ተስህቦዬ እውነታውን መናገር እችል ነበር፡፡ ነገር ግን ያንተ ጭቆናና ኢ-ምክንያታዊ ጥላቻ እና ፍረጃ ቀን ከሌት እያቃዠ ወኔዬን አሳጥቶኛል፡፡ ለሕይወቴ እፈራለሁ ፣ በፍርሃት እኖራለሁ፡፡
ምህረትህን እና ፍቅርህን እየለመንኩ አይደለም፡፡ በአንድ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ እንኖራለን ፤ “የተለመደውንም” ነገር በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ እረዳሃለሁ፡፡ ነገር ግን ሕይወቴን በነፃነት እኖር ዘንድ ተወኝ፡፡ ወንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኔን እና መሬት የምታፈራቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ለእኔም እንደሚገቡ ልነግርህ ነው ይህን ማለቴ፡፡ አሁን ያለኝን ማንነቴን መርጬ አላመጣሁትም፡፡ በዚሁ መልክ የተፈጠርሁ ሰው ነኝ፡፡
ውድ አንባቢ፣ የመጨረሻ ቃሌን እነሆ፡- ወደድክም ጠላህም እኔ አሁንም ያ ትሑት፣ ጎበዝ እና አፍቃሪ ወንድምህ ነኝ፡፡ የሥራ ባልደረባህ ነኝ፡፡ ልጅህ፣ አለቃህ፣ ሠራተኛህ፣ አስተማሪህ ፣ ጎረቤትህ እና ጓደኛህ ነኝ፡፡ ምንም ቢሆን ላንተ ያለኝ ፍቅር ገደብ የለሽ ነውና በማንኛውም ጊዜ አብሬህ መሆኔን እቀጥላለሁ፡፡ የተለየ ተጨማሪ ነገር ካንተ ለማግኘት አልጠይቅም፡፡ ኢ-ምክንያታዊ እና ፈራጅ መሆንህን ብታቆም በጣም ደስተኛው ሰው እኔ እሆናለሁ፡፡ ፆታዊ ተስህቦዬ በመሃላችን ገብቶ ግንኙነታችንን እና ጓደኝነታችንን እንዲያበላሸው አትፍቀድ፡፡ በቅርቡ እኔን የመሰሉ ጓደኞች አግኝቼ በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ ሕይወትን መምራት ጀምሬአለሁ፡፡ በጭፍን ጥላቻህ እንዳታበላሽብኝ ልለምንህ፡፡ ጥላቻ አስቀያሚ ጠባሳን ፣ ፍቅር ደግሞ የሚያምሩ ትዝታዎችን ይፈጥራሉና፡፡ ውድ አንባቢ፣ እንደኔ እንደኔ እስከ ሞት እወድሃለሁ፡፡ ፍቅር ያሸንፋል፡፡
ያንተው፣
ያልታወቀ 7
ፍትሕ
ታሪኬ ብዙ ነው. . . ድርሳነ ግሩም፥ መልክአ ፍቅር፥ ተአምረ ሕይወት፥ ታሪክ፥ ፍልስፍና፥ ሥነ ሕይወትና የሥነ አእምሮ ኩነቶችን አወጋችኋለሁ፡፡
ስሜ ግሩም ይባላል። “ስምን መልአክ ያወጣዋል” እንደሚል ያገሬ ሰው ዓለምን የማይበት መንገድ የተለየና ለወደድኩት የሚሸነፍ ርህሩኅ ልብ እንዲሁም ያቀድኩትን ለማሳካት እስከ ጥግ የሚዋጋ ጠንካራ ልብ ያለኝ “አልፋ ወንድ” ነኝ። አሁን የሃያ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ነኝ፤ ልጅነቴ እጅግ አስደሳች ነበር። እድገቴ ቁርስ፣ ምሳና እራት ከሚበሉ ከድህነት ትንሽ ከፍ ያሉ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ሰባት “A” እያመጡ አንቱ የተባሉ እህቶችና ወንድሞች ሲኖሩኝ እኔ የመጨረሻና ስምንተኛ ልጅ ነኝ። አባታችን ነፍሱን ይማረውና ጥሩ ሥነ ምግባር የነበረው በደንበኖቹም እጅግ የሚወደድ ጠንካራ ነጋዴ ነበር። እናቴ የቤት እመቤት ናት። ውዷ እናቴ ከቤተ ክርስቲያን ቤት፣ ከቤት ቤተ ክርስቲያን እየተመላለሰች ትዳሯን ልጆቿ ያደረገች፥ በልጆቿ አልፎላት እንኳ ልጆቿን የእውቀት ወንዝ ውስጥ ነክራ “የቴሌቭዥን ሪሞት” አስማት የሚሆንባት ሲበዛ ደግና የዋህ ኢትዮጵያዊት እናት ናት።
ለተመሳሳይ ፆታ የተለየ የፍቅር ስሜት ከልጅነቴ ጀምሮ ነበረኝ። ታላላቅ ወንድሞቼን በስፖርት የዳበረ ሰውነት ከማድነቅ ጀምሮ የታዋቂ ስፖርተኞችን ውብ ሰውነት የያዙ ሥዕሎችን በተለየ ስሜት እሰበስብ ነበር።
በመጀመሪያ ጊዜ በፍቅር ይፈትኑኝ የነበሩት ወንዶች መምህሮቼ ነበሩ። በትምህርቴ ኮከብ ተማሪ ስለ ነበርኩ ከመምህሮቼ ጋር ጥልቅ ቅርበት ነበረኝ፡፡ በተለይ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ለባዮሎጂ መምህሬ እጅግ የተለየ ስሜት ነበረኝ። በዚህ ጊዜ ዕድሜዬ ገና አሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ጌይ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ፈጽሞ የማናውቅበት ጊዜ ነበር። አባቴ ሃይማኖተኛ ስለ ነበር እኔና ታላቅ ወንድሜን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችንን ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት እንድንከታተል አደረገን። እዚህ ትምህርት ቤት መማሬ በሃይማኖት በምግባር ምሉእ እንድሆን ረድቶኛል። እስካሁን በሕይወቴ ውስጥ ራስን ከሚጎዱ ልማዶች እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጣጣትና የዕፆች ሱስ የለብኝም። ለዚህም ቤተሰቦቼና ይህ ትምህርት ቤት ባለ ውለታዎቼ ናቸው። የልጅነቴንም ሆነ ወጣትነቴን እረፍት ሰዓት ልክ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና በበጎ አድራጎት እሳተፍ ነበር።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረኝ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር እዚህም ነበር። አሥራ አንደኛ ክፍል ስገባ አባታችንን በሞት ያጣንበት ወቅት ስለ ነበር ከኳስ ጨዋታና ከማኅበረሰባዊ ተሳትፎ ተቆጠቤ የቴኳንዶ ሥልጠና አዘወትር ጀመር። ያኔ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ እንደ አፈቀርኩት መምህሬ አሁንም አብሮኝ ይሠለጥን ከነበረው ጓደኛዬ ብሩክ ጋር ተዋደድን። እንላፋ ነበር. . . ጉንጭ ለጉንጭ እንሳሳም ነበር። ጓደኞቼ “እከሌን አፈቀርኳት . . . በጣም ነው የምወዳት” ብለው ስለ ተቃራኒ ፆታ የፍቅር ታሪካቸውን ሲነግሩኝ እኔ ግን የማስበውና የምናፍቀው ሰው ብሩክ ነበር።
በወቅቱ ያረጋጋኝና ከጓደኞቼ የተለየሁ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ የነበረው በዚህ ጥቅስ ይህ ነበር፦
“ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔስ ለአንተ እጨነቃለሁ፤
በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበር፤
ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ።” 2ኛ ሳሙ. 1፥26
ይህ ጥቅስ ነብዩ ዳዊት ለወዳጁ ዮናታን እንዲህ የጠለቀ ፍቅር ካለው እኔም ወንድሜን ብሩክን እንዲህ ከልቤ መውደዴ ሊያስጨንቀኝ እንደማይገባ አእምሮዬን አሳምነው ነበር።
ወደ ተመደብኩበት ዩኒቨርሲቲ ስገባ ለኢንተርኔት የተሻለ አቅርቦትና ስለ ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እውቀቴ ይጨምር ጀመር። ዩኒቨርሲቲ ልዩ ቦታ ናት፤ ቤተሰቦቼ አጥብቀው እንደ መከሩኝ ራሴን በመንፈሳዊ ሕይወትና በግቢ ጉባኤዎች ተሳትፎ ጀመርኩ። በተመሳሳይ ፆታ ፍቅር የተያዘ ሰውን ቡ*ቲ፣ ግብረ ሰዶማዊ ወይም በእንግሊዝኛው Gay ተብለው መጠራታቸው እጅግ ያስጨንቀኝ ጀመር። ቡ*ቲ የሚለውን ስድብ ከልጅነቴ ጀምሮ የመሃይሞች ስድብ እንደ ሆነ ይሰማኝ ነበር፤ እጅግ የምጸየፈው ቃል ነው። እኔ ዘመኔን ሁላ ወንድ ልጅን መውደዴ ግብረ ሰዶማዊ ለምን ያስብለኛል ብዬ አምርሬ የጮህኩባቸው ጊዜያቶች ይከሰቱ ጀመር።
“ግብረ-ሰዶም” የሚለውን ቃል ለመጀመረያ ጊዜ ያወቅሁት ልጅ እያለሁ በሰንበት ትምህርት ቤታችን መምሬ አባ ፍሬ ስብሐት ሲያስተምሩን ነበር።
አባ በአስፈሪና ሞገስ ባለው ወፍራም ድምጻቸው እንዲህ ነበር ያስተማሩን:- “ልጆችዬ፣ ሰዶምና ገሞራ በዮርዳኖስ ሸለቆ የተቆረቆሩ ከተሞች ሲሆኑ ይኖሩባቸው የነበሩ ሰዎች እጅግ ኃጢአተኞች በተለይ በዝሙት ሥራቸው እጅግ አስጸያፊ ስለ ነበር ፈጣሪ በእሳት ዲን አጠፋቸው። ሰዎች ፈጣሪን መፍራትና ማምለክ ሲተው፥ ለጣዖታት ሲሰግዱ የዚህ ክፉ መንፈስ ያድርባቸዋል።”. . . በማለት ሰፊ ትምህርት ከዘፍ.18-19 ያለውን ታሪክ ይነግሩን ነበር። እኔ ግብረ ሰዶም የሚለውን ቃል እጅግ ስለምጠላውና ይበልጥ ለማወቅ የታሪክ ማኅደርን መፈተሽ ጀመርኩ። ሰዎች “ግብረ ሰዶም” ብለው የሚጠሩት ነገር የሰዶም ነዋሪዎች ከመኖራቸው በፊት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ4000-3000 ዓመተ ዓለም በፊት ግሪኮች እንደ ጀመሩትና በተለይ በእነ አሪስቶትልና ፕሉቶ በደንብ እንደ ተስፋፋ ታሪክ ይናገራል። በሁለተኛ ደረጃ የጀመሩት ሮማውያን ነበሩ። ሮማውያን ግዛትን ከማስፋፋት ጋር የማያባራ ጦርነት ውስጥ ይገቡ ስለ ነበር ወታደር ከወታደር የተመሳሳይ ፆታ ወሲብ መፈጸም ልምድ አድርገውት ነበር። በሦስተኛ ደረጃ በታሪክ የተመዘገበው ግብፃውያን እንደ ሆኑ ነው። ዛሬም ድረስ ማስረጃ ሆኖ የሚታየው በፒራሚዶቻቸው ላይ ወንድ ከወንድ ሲሳሳም የሚያሳይ የመቃብር ቅርጾች አሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ነኝ፤ ሳነበው ለእውቀት ብቻ ሳይሆን ለሕይወት ምነው። አንድን ወንድ ልጅ ስላፈቀርኩ ስለ ምን “ግብረ-ሰዶማዊ” እባላለሁ? በትንቢተ ኤርሚያስ 23:14 ላይ እንዲህ ይላል “በኢየሩሳሌም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥ ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሀሰትም ይሔዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ” ይላል።
አመንዝራነት፣ ሀሰተኝነትና ክፋትን ማበረታታት እንደ ተጠቀሰ አስምሩበት! በትንቢተ ሕዝቅኤል 16:49 ላይ “እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበር፤ ትዕቢት፣ እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበር፤ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም።” ይላል። እዚህ ላይ ደግሞ ትዕቢት፣ ልክ ያለፈ ጥጋብ፣ ሥራ መፍታትና ችግረኛና ድሀን አለመርዳት የሰዶም ኃጢአት እንደ ነበር ተጠቅሷል። ታዲያ አመንዝራነት፣ ሴሰኝነት እና ክፋትን ማበረታታት፣ ትዕቢት፣ ልክ ያለፈ ጥጋብ፣ ሥራ መፍታትና ችግረኛና ድሀን አለመርዳት የሰዶም ኃጢአቶች ከሆኑ አንድን ወንድ ልጅ ስለ ወደድኩ ብቻ ስለ ምን ግብረ ሰዶማዊ እባላለሁ? ከእነዚህ ከተዘረዘሩት ኃጢአቶች ሁሉ ሊነጻ የሚችል ከአርባ ቀን ሕፃን ውጪ ማን ሊኖር ይችላል? ስለዚህ እኔ ግብረ ሰዶማዊ አይደለሁም፥ ነህ ካልከኝ ደግሞ አንተም ስለ ማመንዘርህ፣ ስለ መዋሸትህ፣ ስለ ትዕቢትህና ሌሎችም አንተም ሁነኛ ሰዶማዊ ነህ ማለት ነው!
ጌይ የሚለው ቃልስ እኔን ይገልጸኛል? ጌይ (gay) የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ከ1960 በፊት የሚያስደስት ወይም ደማቅ የሚል ትርጉም ነበረው፤ አሁን ግን የድሮው ትርጉም ቀርቶ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ስያሜ ሆኗል። ስሙ የፈረንጅ መሆኑና ሀገራዊ ቃል አለመኖሩን አስበህ ይህንን ልምድ ከፈረንጅ የወረስከው ነው እንዳትለኝ! እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውጪና ከቪድዮ ካሴት፤ ፊልሞች ውጪ የማየው ነገር አልነበረም። በቪዲዮ የምናያቸው የነጄትሊ፣ ቫንዳም፣ ጄኪቻን ከዛም ከዘለለ የህንድ ፊልም ነበር። እነዚህ ደግሞ የተቃራኒ ፆታ ላይ እንጂ የተመሳሳይ ፆታ ምንም ድርሻ መቸት ያልነበራቸው የባሕር ማዶ ፊልሞች ነበሩ።
አንድ ቀን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከጓደኞቼ ጋር ቁጭ ብለን አንዱ ጓደኛችን ወደ አንዱ የግቢ ተማሪ ጠቁሞን “አያስጠላም ፥ቡ*ቲ እኮ ነው!” ሲል እኔ ልጁን ይበልጥ ማየት ጀመርኩ። ሲኒየራችን ሲሆን የበዛ ቆንጆና የበዛ ሴታሴት ነበር። እኔ ከማርስ እርሱ ከቬነስ እንመስል ነበር። የፋሽን ሽቅርቅርነቱና ቁንጅና በጣም ሲበልጠኝ እኔ ግን የወንዳወንድ ባህርይን በስፖርት በዳበረው ሰውነቴ እጅግ ከእርሱ እለይ ነበር። ስለ ጌይዎች ይበልጥ ማወቅና እኔ ከእርሱ ምድብ ልሆን አልሆን ብዬ መመርመር ፈለግሁ፤ ከኢንተርኔት እስከ የተለያዩ መጽሐፎች ማገላበጥ ጀመርኩ። ምርጫዬ ነው? (My choice?) አንዳንዶች ሰዎች ወደውና ፈቅደው ጌይ ይሆናሉ ብለው ያምናሉ። በባህላችን ነውር፣ በሃይማኖታችን ኃጢአትና በሕጋችን ወንጀል ሆኖ እንዴት ወድጄና ፈቅጄ ጌይ እሆናለሁ? የወላጆች ተጽእኖ (Parents?) የአባት ፍቅር የራቃቸውና በእናት ብቻ ያደጉ ልጆች ጌይ የመሆን ዕድላቸው ይሰፋል ይላሉ። እኔ የአባትና የእናት ፍቅርን ከማየት በተጨማሪ ሳጠፋ እየቀጡ ስጎብዝ እያበረታቱኝ ያደግሁት! ስለዚህ ይህም አይመለከተኝም። የወላጆቼ ተጽእኖ፣ መንፈሳዊነት፣ ታላላቆቼን ማክበርና መታዘዝ፣ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ነበር።
የኋላ ታሪክ (My History?) በሕፃንነት ጊዜ የመደፈር ወይም የማባለግ ሁኔታ የደረሰባቸው ልጆች ጌይ ይሆናሉ ይላል። እኔ እንኳን ልደፈር ቀርቶ እንጁን ያነሣብኝ የለም፤ ስለዚህ ይህም እኔን አይወክልም! አእምሮዬን የሴት ጓደኛ መያዝ እንዳለብኝና እኔ STRAIHT እንደ ሆንኩ ፎገርኩት።
የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ውብና ማራኪ ከሆነች ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመርን። አንዳንድ ጓደኞቼ ውጤታቸው በፆታዊ ፍቅር ውዥንብር የተነሣ ከትምህርታቸው ተሰናክለው ከዩኒቨርሲቲ እንደ ተባረሩ (እንደ ተጫሩ) ስለማውቅ ብዙ ፊት አልሰጠኋትም ነበር፤ “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ይባል የለ? የምኖርባት ዓለም አደገኞች የበዙባት፣ ዋይታና ጩኸት የማያጣት ልዩ የጦርነት ቀጠና ብትሆንም እኔና ሊድያ በሰማይ እንደምኖር ያህል የሞቀና አስደሳች የፍቅር ግንኙነት ቀጠልን። ልቤና ዓይኖቼ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ወንዶች ቢሳቡም የፍቅር ኃይል ፈቃድን ይገዛልና እታመንላት ነበር። አንድ ቀን አብረን እንድናድር ስትጠይቀኝ እኔ ከጋብቻ በፊት ልናደርግ እንደማይገባንና መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙትን እንደሚያወግዝ ነገርኳት። አንድ ቀን በጣም ለምቀርበው ጓደኛዬ ከእጮኛው ጋር ስለሚፈጽመው የፆታ ብልግና ሲነግረኝ ስሜቴን አነሣሳው። ጥዬው ወደ እነሊድያ ዶርም ሄጄ ይዣት ወጥቼ . . . ፍትወተ ሥጋ፣ አንሶላ መጋፈፍ ወይም ወሲብ የሚባለውን የፍቅር ጭማቂ ጠጣሁ፤ ድንግልናዬን አስረከብኩ። ምንም ራሴን በሊድያ ውስጥ ደብቄና ሸሽጌ ብኖርም እኔ ግን ጌይ እንደ ሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አምስተኛ ዓመት ሲሆን ሊድያ ወደ ካናዳ ስትበር እኔም ትምህርቴን ወጥሬ ያዝኩ። ፈጣሪም ፈቅዶ በጥሩ ውጤት ተመረቅሁኝ፤ ብዙም ሳልቆይ ሥራ ያዝኩ። ሴት ልጅ ውበት ናት፣ ፍቅር ናት፣ ስኬት ናት፣ ጣፋጭ ናት፣ ሕይወት ናት፣ ለኑሮህም እጅግ ታስፈልግሃለች። ጥያቄው ግን ሰዎች ቡ*ቲ፣ ግብረ-ሰዶማዊ፣ faggot ወይም ጌይ ይሉኛል ብዬ የዚችህን ሰብለ ወንጌል የተባለችውን ፍጡር ከእኔ ጋር አስሬያት አንተን ፈርቼ በዛብህን ላሳጣት? እስኪ ፍረድ!!!
አንዲትን ሴት ጠብሼ ወይም አግብቼ ራሴን STAIGHT ነኝ ብዬ መፎገር አልፈልግም፤ ከሀገሬም መሰደድ አልሻም። አምላኬን ይህን ስሜት ይወገድልኝ ብዬ ብዙ ጣርኩኝ፤ ብዙ ጸለይኩ. . . ብዙ ጾምኩ. . . ብዙ ገዳማት ሄጄ ጸበል ተጠመቅሁኝ። ልሽሽ በጣርኩ ቁጥር ይብስ እፈተን ጀመርኩ። በስተመጨረሻ በሁሉ ነገር ተስፋ ስቆርጥ ከምኖር ብሞት ይሻለኛል ብዬ አጓጉል ነገሮችን ያደረግሁባቸው ጊዜያትን ሳስብ አሁን ፈገግ ያስብለኛል። “ሞቼ ብገላገልስ” ያልኩባቸው ጊዜያቶችን እንዴት አለፍኳቸው መሰለህ… ዓይን የፈጠረ አምላክ ያያል፥ ጆሮን የፈጠረም ይሰማልና እጸልይ ነበር። ጸሎት ጭንቀትህን አውጥተህ በመናገር እፎይታ የምታገኝበት መንገድ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ልብህን እንድታፈስለት” ከሚፈልገው በሰማይ ካለው አባትህ ጋር የምትገናኝበት መንገድ ነው፤ እርሱ አባቴ አበሳ ጉድን ሸፋኝ ነውና ቅረበው። የሚሰማኝን ነገሮች ለጓደኞቼ፣ ቤተሰቦቼና ለእኔ ለሚያስቡና ያስጨነቀኝ ነገር ትኩረት ሰጥተው ለሚያዳምጡኝ ሰዎች በመናገሬ እጅግ ተጠቅሜአለሁ። ያስጨነቁኝ ሁኔታዎች ምንም ተስፋ የሌላቸው ቢመስሉም ውሎ አድሮ ነገሮች ተለውጠው ይኸው ይህንን ለመጻፍ በቅቻለሁ! ዝናብ እንዳዘለ ደመና የኀዘን ስሜትም ውሎ አድሮ ማለፉ አይቀርምና አንተም ወንድሜ ተስፋ አትቁረጥ። አንተኮ ማለት ከእነዛ እጅግ ብዙ ከሆኑት የአባትህ የስፐርም ሴሎች ሁሉ ቀድመሃቸውና አሸንፈህ ወደ እናትህ ማሕጸን ገብተህ እጅግ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ነፍስ ዘርተህ በእውቀትህና በጥበብህ ዓለምን ልትቀይር የምትችል ሰው ነህ! ተራራ ሲወጡት ያደክማል፤ ሲጨርሱት ግን ከፍታ ላይ ያደርሳልና አትከፋ. . . አትዘን. . . ተስፋ አትቁረጥ።
አንተስ ወንድሜ ስለ ምን አብዝተህ ትጠላኛለህ? ሁሉ ነገር ገደብ አለው፤ የማያልቀው መልካም ነገር እንጂ ስድብም ንቀትም ያልቃል። ለምን የማያልቀውን አትመርጥም? ራስ ኃይሉ ለማእከላዊ መንግሥት ግብር ለመሰብሰብ በጎጃም ሕዝብ ላይ አንድ አንድ ብር ግብር ጣሉበት። አንዲት ሴትም ቢያዝኑልኝ ብላ፦ “ይህን ገንዘብ ያመጣሁት ውሃ ሽጬ ነው” አለች። ራስ ኃይሉም “ተቀበላት፣ ተቀበላት፣ አንቺማ የያዝሽው የማያልቀውን ነው” አሏት ይባላል። ደጉ መቼ አልቆ ክፉ ትናገረኛለህ? ፍቅር መቼ አልቆ ትጠላኛለህ? ደግ ነገር አያልቅም፤ ክፋት ግን ያልቃል። ፍቅር የሌለው አረመኔ መንግሥታት ሁሉ ስለ ፈጸሙት የግፍ ግድያ የድጋፍ ፊርማና ሰልፍ ይፈልጋሉ። ፈጣሪ ግን ስለ ሰዶምና ገሞራ ቅጣቱ አድናቆት ብታቀርብለት ሰልፍ ብትወጣ እኔን የሚያስደስተኝ ቢመለሱልኝ ነበር ይልሃል። ፈጣሪ የፈጠረውን ሰው በመናቅ፣ አምላክ ተስፋ ባልቆረጠበት ላይ ተስፋ በመቁረጥ፣ ጌታ ባልፈረደበት ላይ በመፍረድ ስለ ምን ትበድላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” ይላል (1ጴጥ. 2:17)። ስለዚህ ለእኛ ጥላቻ ሊኖርህ አይገባም. . . ስለዚህ ጸልይልኝ!
ፍትሕ ይውረድ!
አመሰግናለሁ!
♠ ABOUT ♠
We would love to be able to share biographies of the authors who have contributed to this collection of short stories but safety must come first.
To those named and anonymous, we are grateful for trusting us with you personal stories.
♥HOUSE OF GURAMAYLE ♥
House of Guramayle is a collaborative intersectional platform created by exiled Ethiopian activists based around the world. We aim to advocate for the Ethiopian LGBTIQ+ community and create a safe space for them to share their stories and experiences of social, economic, health and political issues.
Do you need help?
We have a directory of resources for Ethiopian LGBTIQ+ community members in danger.
Resources