Letter to my parent series #2
Blog | 20.09.22
ለውድ አባቴ መለሰ ስብሐት:-
እንደምን ሰንብተሃል? ሰማይ ቤት ምቹ ነው ወይ? ጤናህስ ይጠበቃል? ጀርባህ ላይ ዳዴ እየሄደች የምታሽልህ ልጅ አለች? ካልሲህንስ የምታጥብልህ? ያነበበችውን ታሪክ እና መንገድ ላይ ያየችውን ሁሉ ካልነገርኩህ ብላ የምታደርቅህስ?
የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ መሄድህን ስሰማ አብልጦ ያሳዘነኝ ለዘላለሙ መለያየታችን ሳይሆን ሳንነጋገር መሄድህ ነው። በሞት መለያየት ማናችንም ልናስቆመው የማንችለው የተፈጥሮ ክስተት መሆኑን እኔም አንተም እናውቅ ነበር። በሕይወት እያሉ መለያየት ግን ሊፈታ የሚችል ቁዋጠሮ ሆኖ ሳለ ሳይፈታ ሲቀር በፀፀት ይሞላል። በተለይ ደግሞ እንዲህ ያለ ቁዋጠሮ የተከሰተው እንደኔና እንዳንተ በሚዋደዱ ሰዎች መሃል ሲሆን ከፀፀት አልፎ ልብ ይሰብራል።
ያንተ ሚስት እና የኔ እናት ሙላቷ፣ እኔ ሶስት ዓመት ተኩል እያለው ካረፈች በሁዋላ፣ እኔና አንተ ለብዙ አመታት ብቻችንን ነበርን። ቢያንስ በኔ አእምሮ ብቻችንን ነበርን። በነዛ አመታት ነው አሉ ለዘመዶቻችን፣ “ይቺ ልጅ ነጻ ሆና እንድታድግ ነው የምፈልገው” ብለህ የተናገርከው። ምናልባት አንተም እያረጀህ ስለነበረ እና ብዙ ግዜም ህመምተኛ ስለነበርክ፣ እንዲሁም እናቴን በማጣቴ፣ አንተን ባጣህ እራሴን ማሳደግ እንዳለብኝ አውቀህ ይሆናል እንደዛ ያልከው። ምክንያትህ ምንም ይሁን ምን ነጻ አድርገህ አሳደግከኝ። ክርክር አስተማርከኝ። አንተንም ጨምሮ ማንኛዉንም ሰው በእድሜ ስለበለጠኝ ብቻ ዝም ብዬ በመስማት ፈንታ፣ ተከራክሬ፣ አውጥቼ አውርጄ፣ ጨምቄ፣ ወደራሴ ድምዳሜ እንድመጣ አበረታታከኝ።
ታዲያልህ አባዬ፣ ኖሬ ኖሬ በሃያ አምስተኛው አመቴ ላይ የሆነ ከባድ ጥያቄ ሲገጥመኝ፣ አንተ ያስተማርከኝን ነጻነት ተጠቅሜ፣ ከራሴ ጋር ተከራክሬ፣ አውጥቼ አውርጄ፣ ጨምቄ፣ ወደራሴ ድምዳሜ መጣሁልሃ። እኔም አንተም የመሰለን፣ የነጻነቴ ክንፍ አብሮ አብሮ በዓለም ዙሪያ ወስዶ መልሶ ግን አንተጋ የሚያመጣኝ ነበር። ለካ ማደግና ነጻ መሆን አንዳንዴ ከሚወዱት አባት ይለያል?
መለያየይት ግን አልነበረብንም። ብንነጋገር ኖሮ፣ አውነቱን አፍረጥርጬ:- “ይሄውልህ አባዬ፣ እኔ ሴት እንጂ ወንድ ማግባት አልፈግም፣ እግዜር ልቤን ሲሰራው የሴት ማደሪያ አድርጎ ነው” ብዬ ብልህ ኖሮ፣ ምናልባት “እሺ እንግዲህ፣ አግዜር ካለ ምን ይደረጋል” ትለኝ ነበር። ወይም ደግሞ በኔ የፍቅር አካሄድ ባትስማማም፣ የተቀረውን ጉዋደኝነታችንን እንቀጥል ነበረ። ነገር ግን ፈራሁ። ከዚህ በሁዋላ ልጄ አይደለሽም፣ ክጄሻለሁ፣ ከፊቴ ተሰወሪ ትለኛለህ ብዬ አልነበረም የፈራሁት። ይልቁንስ በልቤ ውስጥ ያለውን ያንተን ምስል–የጎበዙ አባቴ፣ ሴት ልጁን ነጻ እንድትሆን አድርጎ ያሳደገው ስልጡኑ አባቴ፣ ተጫዋቹ እና ቀልደኛው አባቴ–እንዳላጣው ብዬ ነው። ማለትም:- አንተን ከገዛ ራስህ ላድንህ ፈልጌ።
ትልቅ ስህተት ፈጽሜያለሁ፣ አባዬ። ይቅርታ አድርግልኝ። እውነቱን ነግሬህ እውነተኛ ራስህን እንድትገልጥልኝ ዕድል ልሰጥህ ይገባ ነበር። ይሄኔ እኮ ብነግርህ ኖሮ፣ “ታዲያ አንቺ ሴት ወደድሽ ወንድ እኔን ምን አገባኝ? የኔ ሥራ አንቺን መውደድ ነው። አንቺ ከሌለሽበት ደግሞ ሰማይ ቤት ለኔ ምኔ ነው?” ብለህ ታላቅነትህን ታሳየኝ ነበር። ምናልባት እኮ ብነግርህ ኖሮ፣ በልብህ ውስጥ ያሉ የማፍቀር ችሎታህን የሚያሳንሱብህን እንቅፋቶች ሁሉ በኔ ምክንያት ሰባብረህ ወጥተህ እውነትም ልዩ አባት መሆንህን ታስመሰክር ነበር። እኔ ግን በፍርሃቴ ምክንያት ያንን አድል ሳልሰጥህ ቀረሁ።
አንዱ የፍቅር መለያ፣ ለምንወዳቸው ሰዎች ሁሉ በተቻላቸው መጠን እራሳቸውን እንዲገልጡ፣ ውስጣቸውን ያለፍርሃት እንዲያሳዩን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። ምክንያቱም ልብ ለልብ ካልተያየን፣ ልቦቻችንን ማገናኘት አንችልም። ልቦቻችን ካልተገናኙ ደግሞ ጸሎታችን አይሰማም። ጸሎት በሰማይ የሚሰማው አውነተኛ ፍቅር በምድር ላይ ሲኖር ብቻ ነው። እውነተኛ ፍቅር ደግሞ ፍርሃት ባለበት ሊኖር አይችልም። እግዚአብሔር ልብን እና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና፣ ልቦቻቸው በፍርሃት እና በውሸት የተከፋፈለባቸው ቤተሰቦች፣ በከንፈራቸው:- “እግዚአብሔር ሆይ፣ ይሄው በስምምነት፣ በአንድ ልብ፣ አንድ ነገር ፍለጋ ወደ አንተ መጥተናል” ብለው ቢፀልዩ፣ እግዚአብሔር ግን ሊሰማቸው አይችልም።
በኔ ፍርሃት ምክንያት ልባችን እንደተከፋፈለ በመሞትህ በጣም አዝኛለሁ፣ አባዬ። በፀፀት ተጠምጄ ግን በዚች ምድር ላይ የቀረኝን ጌዜ በ “ቢሆን ኖሮ” ቁዘማ አላሳልፈውም። ማንም ልጁን በእውነት የሚወድ አባት ልጁ በሃዘን እየቆዘመች ሕይወቷን እንድታሳልፍ አይፈልግም። ይልቁንስ እንድትኖርለት፣ እንድትሰፋ፣ እንድትለመልም፣ እንድትበር እንጂ። እበርልሃለሁ አባዬ። ልቤን፣ ነፍሴን፣ መንፈሴን በፍቅር ሞልቼ እለመልምልሃለሁ። አንተና ወድንሜ ተድላ ባስተማራችሁኝ የጽሑፍ ችሎታ ተጠቅሜ ደግሞ፣ ሌሎች ልጆች ካባቶቻቸውና ከናቶቻቸው በፍርሃት ምክንያት እንደተከፋፈሉ እንዳይሞቱ አስጠነቅቃለሁ። ልጆችና ወላጆች በግልጽ እንዲነጋገሩ፣ ልቦቻቸውን ከፍተው ያለ ፍርሃት ለርስበርስ እንዲያሳዩ፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በመፍጠርም በእግዜር ፊት የመሰማት ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ አበረታታለሁ። ታየኛለህ ብቻ አባዬ ስኖርልህ። ሰማይ ቤት ያሉ አዲስ ጉዋደኞችህን፣ “እዩ እዩ፣ ያቺ ጎበዝ የኔ ልጅ ነች!” እያልክ ጉራህን እንደምትነዛ እርግጠኛ ነኝ።
ደህና ቆይልኝ!